Fana: At a Speed of Life!

ኢኮኖሚው ውስጣዊና ውጫዊ ጫናዎችን ተቋቁሞ እየተጓዘ መሆኑን አቶ አህመድ ሺዴ ገለጹ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 15፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢኮኖሚው ውስጣዊና ውጫዊ ጫናዎችን ተቋቁሞ እየተጓዘ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ ገለጹ፡፡
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለሙያዎች ማኅበር ትኩረቱን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ አተኩሮ 19ኛውን ዓለም አቀፍ ጉባዔውን እያካሄደ ነው።
የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሺዴ በጉባዔው ላይ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ የሰላም እጦት፣ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት፣ ድርቅ እና የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት በኢኮኖሚው ላይ ከፍተኛ ጫና አሳድሯል ብለዋል፡፡
ይህን በመገንዘብም መንግሥት ችግሮቹን ለመቋቋም የሚያስችለውን ሥራ እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ሀገሪቱ ከፍተኛ የመልማት እምቅ አቅም እንዳላት ጠቅሰው÷ ይህንን ሀብት ለመጠቀምም ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው በትኩረት እየተሠራበት መሆኑን ተናግረዋል።
ሳይንሳዊ ትንታኔዎችን የተከተለ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያዎችን ለመቀበል የገንዘብ ሚኒስቴር ዝግጁ መሆኑንም ነው የተናገሩት።
የልማት ግቦችን ለማሳካት የእዳ ጫናዎችን ለመቀነስ የብድር ሽግሽግ በማድረግ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው÷ ይህም የፊሲካል አቅምን ለማሳደግ እንደሚረዳ ጠቁመዋል።
ማህበሩ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያ ለማድረግ የሚያስችሉ የፖሊሲ ግብአቶችን የሚያቀርብ ከሆነ የገንዘብ ሚኒስቴር ለመቀበል ዝግጁ መሆኑን ገልታ ለእዚህም ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡
የብሔራዊ ባንክ ገዢ ዶክተር ይናገር ደሴ በበኩላቸው÷ የፋይናንስ ዘርፍ ለሀገር ኢኮኖሚ እድገት ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው÷ በፋይናንስ ዘርፉ የአጭር እና የረዥም ጊዜ አቅጣጫ ተይዞ እየተሠራ መሆኑን አመላክተዋል።
የኢንቨስትመንት፣ የግብርና፣ የአምራች ዘርፉ፣ በሚገባ እንዲያመርት ማድረግ ያስፈልጋል፥ ለዚህ ደግሞ የባንኮች ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለሙያዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት ዶክተር ለማ ጉዲሳ÷ ማኅበሩ ለኢኮኖሚ ፖሊሲ መሻሻል አስፈላጊና በጥናት የተመሰረቱ ግብአቶችን እያቀረበ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ጉባዔው ለሁለት ቀናት በሚኖረው ቆይታ÷ በግብርና ኢንዱስትሪ የስራ እድል ፈጠራ፣ የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን በኢትዮጵያ፣ በኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፉን ማሳደግ፣ የግሉ ዘርፍ ዕድገት በኢትዮጵያና ተጽዕኖን የተመለከቱና የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለማሻሻል ያሉ ዕድሎችና ማነቆዎች የሚዳስሱ ጥናቶች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸው ይጠበቃል፡፡
በተስፋዬ ከበደ
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.