Fana: At a Speed of Life!

ኢዜማ በሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከአባላቱና ደጋፊዎች ጋር በሚዛን አማን ከተማ ተወያየ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 9 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) በሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከአባላቱና ደጋፊዎች ጋር በቤንች ሸኮ ዞን ሚዛን አማን ከተማ ውይይት አካሂዷል፡፡

የፓርቲው ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በስፍራው ተገኝተው ኢዜማ ስለሚከተላቸውና በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ለታዳሚዎቻቸው ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ፕሮፌሰር ብርሃኑ የምረጡኝ ቅስቀሳ እና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ከአባላቶቻቸውና ከደጋፊዎቻቸው ጋር ውይይት ለማድረግ ሚዛን አማን ከተማ ሁለገብ አዳራሽ ሲደርሱ አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡

በዚህ ወቅት የፓርቲው ዋና ሊቀመንበር፥ በሀገር አንድትና በሀገር ሰላም ጉዳይ ላይ በአንድነት እንቆማለን ብለዋል፡፡

ሀገር ከሌለ ፖለቲካ የለም፣ ሀገር ከሌለ ዴሞክራሲ የለም ያሉት ፕሮፌሰሩ፥ ፖለቲካ እንዲኖር ከተፈለገ በቅድሚያ የሀገራችን ሰላም መጠበቅ አለበት ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ስለዚህ በሀገር ሰላም ጉዳይ ላይ ከገዥው ፓርቲ ጋር አንድ ነን ማለታቸውን የደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ዘግቧል፡፡

ይሁንና ኢዜማ ከገዥው ፓርቲ የሚለየው ፖለቲካ ከዘረኝነት ወጥቶ በዜግነት ላይ የተመሰረተ መሆን አለበት ብሎ ስለሚያምን ነው ብለዋል፡፡

በየክልሉ የተቋቋመው ልዩ ሀይል የዜጎችን ደህንነት በእኩልነት እየጠበቀ ስላልሆነ ሕዝብ እኛን ከመረጠ የዜጎችን ደህንነት በእኩልነት የሚጠብቅ ጸጥታ ኃይል በሀገር ደረጃ እናቋቁማለን ነው ያሉት፡፡

በሀገሪቱ እየተስተዋለ ያለው የኑሮ ውድነት በአቅርቦት ማነስ ችግር የተከሰተ ስለሆነ ክፍተኛ ቁጥር የያዘውን የአርሶ አደር ማምረት አቅም ለማሳደግ ኢዜማ የመሬት አጠቃቀም ላይ የተሻለ አማራጭ አለው ብለዋል፡፡

ኢዜማ ባልተማከለ አስተዳደር ያምናል ያሉት የፖርቲው ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ብርሃኑ፥ ከታችኛው አርከን ጀምሮ እስከላይ ዜጎች በመረጡት መሪ እንዲተዳደሩ ይደርጋል ብለዋል፡፡

በሚዛን አማን ከተማ ኢዜማ ባካሄደው ውይይት ከቤንች ሸኮ ዞን የተወጣጡ የፓርቲው ደጋፊዎች አባላት እንዲሁም የተጋበዙ እንግዶች የተገኙ ሲሆን፥ የፓርቲው ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ባቀረቡት ማብራሪያ ላይ ከቤቱ አስተያየትና ጥያቄ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበት ተጠናቋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.