Fana: At a Speed of Life!

ከንቲባ አዳነች አቤቤ የስራ ቦታ ላይ ክትትል ለማድረግ ያስችላል የተባለውን የሰራተኞች የጣት አሻራ ፊርማ አሰራርን አስጀመሩ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 26፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ሰራተኞች የመንግስት የስራ ሰዓትን በአግባቡ እንዲጠቀሙ ለማስቻል የጣት አሻራ ፊርማ የማስጀመር ስነ ስርዓት በአዲስ አበባ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ተካሂዷል፡፡

በመርሃ ግብሩ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፥ በከተማ አስተዳደሩ የአገልግሎት አሰጣጡን ለማዘመንና ፈጣን ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሰራተኞች በትክክል የስራ ቦታቸው ላይ መገኘትና አገልግሎት እየሰጡ ስለመሆኑ ለማረጋገጥ በተለያየ የቴክኖሎጂ ስርዓት ተደግፎ እንዲሰራ እየተደረገ እንደሚገኝም ገልፀዋል፡፡

ሰራተኞች የስራ ሰዓት ማረፈድ፣ በስራ ሰዓት በትክክል ስራ ገበታ ላይ አለመገኘት፣ ሁለት ቦታ ተቀጥሮ ደሞዝ መብላት እና ስራ ላይ የሚያደርጉትን ትኩረት በቴክኖሎጂ ደግፎ ክትትልና ድጋፍ ለማድረግ ተጠናቆ የነበረው የጣት አሻራ መሰረተ ልማት ዛሬ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ የጣት አሻራ ፊርማ ተጀምሯል፡፡

የጣት አሻራው፥ ሰራተኛው ጠዋት ቢሮ ሲገባ፣ ቀን ምሳ ሲወጣና እንዲሁም ማታ ከስራ ሲወጣ ይፈርማል ተብሏል፡፡

ይህን በቴክኖሎጂ የተደገፈ የፊርማ አሰራር ሰራተኛው ስንት ሰዓት እንደሰራ ክትትል የሚደረግበትና በቆየባቸው የስራ ሰዓት የሰራቸውን ስራዎች ውጤታማነት የሚለካበት ስርዓት አንድላይ አጠቃሎ የያዘ ነው መባሉን ከአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

 

በተመሳሳይ ከንቲባዋ የልደታ ክፍለ ከተማን አገልግሎት አሰጣጥ፤ የከተማ ግብርና፤ የዳቦ ፋብሪካዎች እና የምገባ ማዕከላት ግንባታ፤የቤት ግንባታ፤  እንዲሁም የሌሎች ፕሮጀክቶችን አፈጻጸፀም  ጎብኝተዋል ።

 

በክፍለ ከተማው  እየተከናወኑ ያሉ ግንባታዎችና ሌሎች ሰው ተኮር ተግባራት በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቁም ከተማ አስተዳደሩ እንቅፋት የሚሆኑ ችግሮችን   በመለየት   በተለየ ሁኔታ ድጋፍ እንደሚደረግ ተናግረዋል ።

 

ከንቲባ አዳነች  ከፕሮጀክቶች ጉብኝት ጎን ለጎን በወረዳዎች ያለውን በአገልግሎት ዘርፉን የሚታዩ  ችግሮችን  የተመለከቱ ሲሆን÷ አገልግልግሎት ፈልገው ከመጡ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት አካሂደዋል፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.