Fana: At a Speed of Life!

ከንቲባ አዳነች አቤቤ የጃራ አባገዳ ት/ቤት ውስጥ ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ ህንጻዎች የግንባታ ስራ የመሰረት ድንጋይ አስቀመጡ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 29፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ የጃራ አባገዳ ትምህርት ቤት ውስጥ ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ ህንጻዎች የግንባታ ስራ ለማስጀመር የመሰረት ድንጋይ አስቀመጡ፡፡

ለተከታታይ ሦስት ዓመታት ሲጠየቅ የቆየውን በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 የጃራ አባገዳ ትምህርት ቤት ውስጥ የተማሪዎች መማሪያ፣ የአስተዳደር ህንፃ፣ የላይብረሪና የላብራቶሪ አገልግሎት የሚውሉ ህንፃዎች ናቸው የሚገነቡት፡፡

ከዚህ ቀደም ከፍተኛ የሕዝብ ጥያቄ ከነበረባቸው አንዱ የሆነው ይህ ትምህርት ቤት፥ ግንባታው ሲጠናቀቅ የቅበላ አቅሙን ከ405 ወደ 1500 በማሳደግ ትልቅ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ተገልጿል፡፡

ከንቲባ አዳነች አቤቤ የመሰረት ድንጋዩን ባስቀመጡበት ወቅት፥ የሕዝብን አንገብጋቢ ችግሮች ቅድሚያ ሰጥተን በመፍታት ሂደት ላይ ነን ያሉ ሲሆን፤ ትምህርት ቤቱም የዚህ ማእቀፍ አንዱ አካል መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ተማሪዎች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው መማር ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያገኘና ሕገ መንግሥታዊም መብት ነው ያሉ ያሉት ከንቲባዋ ፥ በሌሎች የሀገራችን ክልሎችም በበርካታ ቋንቋዎች ትምህርት እየተሰጠ ነው ብለዋል፡፡

አዲስ አበባ ውስጥም ተማሪዎች በአማርኛ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ ዓለም አቀፍ ቋንቋዎች ማለትም በግሪክ፣ በፈረንሳይኛ፥ በአረብኛ፣: በቱርክና በመሳሰሉት እንደሚማሩ ጠቁመው፥ የአገራቸውን ባንዲራ ይሰቅላሉ፤ የአገራቸውንም መዝሙር ይዘምራሉ ፤ ከአገራቸው ቋንቋ አንዱ በሆነው በኦሮምኛም መማር ከጀመሩም ዋል አደር ብለዋል ነው ያሉት፡፡

ሆኖም ግን አንዳንዶች ይህንን እንደ ስህተት በመቁጠር የፖለቲካ አጀንዳ ሊያድረጉት መሞከራቸው ተገቢ አለመሆኑን ገልጸው፥

ሕፃናት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው መማርና መናገር ሙሉ መብት እንዳላቸው ገልጸው፥ ልጆች በመብታቸው እንዳይጠቀሙና እንዲሸማቀቁ የሚያደርጉ አካላት ከህገ ወጥ ድርጊታቸው እንዲታቀቡም አሳስበዋል፡፡

አዲስ አበባ ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካውያን እና ለዓለም አቀፍ ተቋማት መልካም ቤት ሆናለች ያሉት ከንቲባ አዳነች ፥ የራስዋን ልጆች የምታሸማቅቅ እንድትሆን ለማድረግ የሚጥሩ አካላት መሰረታዊ ስህተት እየፈፀሙ ስለሆነ በፍጥነት መታረም አለባቸው ሲሉ በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡

ዘላቂ ሰላምና ልማት የሚመጣው ህዝቡን አስተባብሮና አንድነቱን አጠናክሮ በመምራት እንጂ የጥላቻን አስተሳሰብ በመዝራት አይደለም ነው ያሉት ከንቲባዋ፡፡

የትምህርት ቤቱ ግንባታ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ ለአገልግሎት እንደሚበቃ መግለጻቸውንም ከከንቲባ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.