Fana: At a Speed of Life!

ከፍተኛ የክረምት ዝናብ በሚያገኙ አካባቢዎች ጥንቃቄ እንዲደረግ ግብርና ሚኒስቴር አሳሰበ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 29፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በመጪው ክረምት ወቅት ከፍተኛ ዝናብ በሚያገኙ አካባቢዎች የሚኖሩ አርሶ አደሮች የጎርፍ መቀልበሻ ቦዮችን ከወዲሁ በማዘጋጀት ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባ የግብርና ሚኒስቴር አሳስቧል።

ሚኒስቴሩ ከብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት የሚወጡ  ትንበያዎችን ለአርሶ አደሩ ተደራሽ  እያደረገ  መሆኑንም አስታውቋል።

የኢንስቲትዩቱ የአየር ሁኔታና  የአየር ጠባይ ትንበያ ባለሙያ ታምሩ ከበደ እንደገለጹት÷ ላሊና ባስከተለው የአየር ጠባይ ለውጥ በበልግና መኸር ወቅቶች ደረቃማ  ወራት በዝተው እንዲስተዋሉ አድርጓል።

በክረምት ወቅትም በተለይ በሐምሌና ነሐሴ ወር ከመደበኛ በላይ ዝናብ እንደሚኖር ትንበያዎች መጠቆማቸውን ጠቅሰው÷ በዚህም በአርሶ አደሩ ማሳ ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ከወዲሁ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

በሚኒስቴሩ የሰብል ልማት ዳይሬክተር ኢሳያስ ለማ በበኩላቸው÷ በመጪው ክረምት በሚኖረው ዝናብ በአንዳንድ አካባቢዎች ጎርፍና የመሬት መንሸራተት አደጋዎች ሊከሰቱ እንደሚችሉ  አመላክተዋል፡፡

በዚሁ ወቅት የተሻለ የሰብል እድገት እንደሚጠበቅ ጠቅሰው÷ አርሶ አደሩ የአረም ቁጥጥር ሥራውን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ማሳሰባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በተለይ ከማሳ ውጭ የሚሰሩ የአፈርና ውሃ ጥበቃ፣ የውሃ መቀነሻና የጎርፍ መቀልበሻ ቦዮችን ማዘጋጀት ጨምሮ ተመሳሳይ የመከላከያ ዘዴዎችን መተግበር እንደሚገባም ነው ያነሱት።

አርሶአደሩ በበልግ የመጨረሻው ወቅት የሚኖረውን ዝናብ ለክረምት ማሳ ዝግጅት መጠቀም አለበት ያሉት አቶ ኢሳያስ÷ የዘር ወቅት በመሆኑ ማሳን በዘር ለመሸፈን ጠንክሮ መሥራት እንደሚጠበቅበትም መክረዋል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.