Fana: At a Speed of Life!

ኮርፖሬሽኑ የመንግሥት ሠራተኞችን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመፍታት የሚያግዝ የግንባታ አማራጭ መርሀ ግብር አስተዋወቀ

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 20 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የመሬት ባንክና ልማት ኮርፖሬሽን የመንግሥት ሠራተኞችን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመፍታት የሚያግዝ የግንባታ አማራጭ መርሀ-ግብር ለባለድርሻ አካላት ማስተዋወቂያ የምክክር ጉባኤ አካሂዷል።

የኢፌዴሪ የመሬት ባንክና ልማት ኮርፖሬሽን “ኦቪድ ኮንስትራክሽን” ከተሰኘው ሀገር በቀል ኮንስትራክሽን ድርጅት ጋር በመንግሥትና የግል ዘርፍ ትብብር ስልት በመኖሪያ ቤት ችግር ውስጥ ላሉ የፌዴራል የመንግሥት ሠራተኞችና ሌሎች ተጠቃሚዎች ዘላቂ መፍትሄ መስጠት የሚያስችል የግንባታ መርሀግብር ለባለድርሻ አካላት አስተዋውቋል።

የኮርፖሬሽኑ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሌንሳ መኮንን በመድረኩ ላይ እንደገለጹት፤ መርሀግብሩ በዋነኛነት የመክፈል አቅም የሌላቸውንና በዝቅተኛ ወርሃዊ ገቢ የሚተዳደሩ የመንግሥት ሠራተኞችን ተጠቃሚ ያደርጋል።

ከቤት ኪራይ ዋጋ ንረትና የኑሮ ሁኔታ ምቾት ማጣት ለማላቀቅ አማራጮችን ለማስፋት የተቀረጸ መርሃ ግብር እንደሆነም ተናግረዋል።

የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽነር አቶ በዛብህ ገብረየስ በበኩላቸው መርሃ-ግብሩ በመንግሥት አገልግሎት ዘርፍ (ሲቪል ሰርቪሱ) የሪፎርም ፕሮግራም ሶስት “የሰው ሀብትና ልማትና አስተዳደር” ስር “ከስራ ከባቢ ምቹነት ፕሮጀክት” ጋር በቀጥታ ተያያዥነት እንዳለው ገልጸዋል።

የመፍትሄ እርምጃውም ለሠራተኞች መኖሪያ በማመቻቸት ጤናማ፣ በኑሮ ሁኔታው የተረጋጋ እና ምርታማ የሰው ሀብትን ለማጎልበት እንደሚጠቅም አመላክተዋል።

አያይዘውም የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም ፕሮግራሙ “ትልቅ ዋጋ ለሰው” በሚል መርህ የተቀረጸ እንደመሆኑ፣ ሃገራዊ ለውጡ የሲቪል ሰርቪስ ዘርፍን ለማዘመን ትኩረት መስጠቱ ገልጸው፤ እንደዚህ ዓይነት መርሀ ግብሮች ሲቪል ሰርቪሱን በማዘመን ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.