Fana: At a Speed of Life!

ዜጎች ከፋፋይ ሀሰተኛ መረጃዎች ራሳቸውን ሊጠብቁ ይገባቸዋል-ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ

አዲስ አበባ፣ ጥር 7፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ)  ዜጎች ከፋፋይ ከሆኑ ሀሰተኛ መረጃዎች ራሳቸውን በመጠበቅ ኢትዮጵያን መገንባት ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባቸው በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ ገለፁ።

 

ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ አሸባሪው ህወሓት ባለፉት ወራት በአማራና አፋር ክልሎች ወረራ በማካሄድ ከፍተኛ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ስነ-ልቦናዊ ጉዳት ማድረሱን ተናግረዋል።

 

ኢትዮጵያዊያን በህብረ-ብሄራዊ አንድነት በጋራ ተሰልፈው ወረራውን መቀልበስ መቻላቸውን አንስተው፤ “ኢትዮጵያን አፈርሳለሁ” ብሎ የተነሳው የሽብር ቡድን በመከላከያ ሰራዊትና ሌሎች የፀጥታ ሀይሎች የተቀናጀ ዘመቻ ክፉኛ ተመትቶ ከወረራቸው አካባቢዎች መውጣቱን ተናግረዋል።

 

የጠላት አከርካሪ የተመታው በኢትዮጵያዊያን የተባበረ ክንድ እንደመሆኑ መጠን ድሉ ኢትዮጵያዊያን በጋራ ያመጡት መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል ብለዋል።

 

የተገኘውን ድል ለቀጣይ ሰላም እና ልማት እንዲሁም አገር ግንባታ መጠቀም በሚቻልበት ሁኔታ ላይ በየደረጃው ያለ አመራር ውይይት ማድረጉን ገልፀዋል።

 

ከህግ ማስከበር እስከ ህልውና ዘመቻው የታየውን ተናቦና ተቀናጅቶ የመስራት አቅም ለመልሶ ግንባታ መጠቀም ይገባል ብለዋል።

 

በህብረ-ብሄራዊ አንድነት የተገኘውን ድል ከምንም ጊዜ በላይ ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑን አስታውሰው፥ የውይይት ዓላማም ድሎቻችንን ተጠቅመን አገራችንን እንዴት በጋራ እናልማ የሚል መሆኑን አስገንዝበዋል።

 

ኢትዮጵያዊያን ልዩነቶች ሳይገድባቸው ለአንዲት ኢትዮጵያ በጋራ መስዋዕትነት በመክፈል በብዝሃነት ውስጥ አንድነታቸው የጠነከረ መሆኑን ማሳየታቸው በውይይቱ መነሳቱን ገልፀዋል።

 

ይህን የተፈጠረውን አቅም ከድል በኋላ በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ በመገንባት ስራ ማዋል የሁሉም ሀላፊነት ሊሆን ይገባል የሚል ሀሳብ መነሳቱንም አብራርተዋል።

 

ህብረ-ብሄራዊ አንድነት እንዴት እንገንባ፣ የተገኘውን የአመራር ቁርጠኝነት እንዴት እናስቀጥል፣ በሚዲያና ኮሚኒኬሽን ጠንካራ የህዝብና የመንግስትን ግንኙነት እንዴት ይጠናከር የሚሉት የቀጣይ ስራዎች ተብለው የተለዩ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

 

በመንግስትም ሆነ በግል ቁጠባን መሰረት ያደረገ የአኗኗር ዘይቤ መከተል፣ የድህረ ጦርነት ኢኮኖሚ መገንባት እና በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ የመገንባትና የማቋቋም ስራዎችን ሁሉም በሀላፊነት ወስዶ መስራት እንዳለበት በውይይቱ ተነስቷል ብለዋል።

 

ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ሰላምና ደህንነት የማይመቻቸው፣ ኢትዮጵያዊያን ሲተባበሩ አንድ ሲሆኑ የማይወዱ አካላት በማህበራዊ ሚዲያ የውይይቱን አላማ ወዳልተገባ መንገድ በመተርጎም ሀሰተኛ መረጃን በማሰራጨት ላይ ይገኛሉ ብለዋል።

 

ኢትዮጵያን መገንባትና ማጠናከር የውይይቱ ዓለማ ሆኖ ሳለ በውይይቱ ያልተዘጋጀ ሰነድ አስመስለው በማዘጋጀት ላልተገባ የፖለቲካ አላማ እየተጠቀሙ መሆኑን አብራርተዋል።

 

በህዝብ መካከል የተፈጠረውን አንድነት ጠላቶች በሀሰተኛ ፕሮፖጋንዳ ለማፍረስ ያዘጋጁት ሴራ በመሆኑ ዜጎች ከፋፋይ ከሆኑ ሀሰተኛ መረጃዎች ራሳቸውን በመጠበቅ ኢትዮጵያን መገንባት ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባቸው አሳስበዋል።

 

ኢትዮጵያዊያን ከሚከፋፍሉን ሀሳቦች በላይ መሆናችንን ማሳየት እንደሚገባንም ጠቁመዋል።

 

 

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.