Fana: At a Speed of Life!

የላሊበላ ቅርስ የሰው ልጆች ሁሉ ሃብት በመሆኑ በጋራ ልንጠብቀውና ልንከባከበው ይገባል-ዶ/ር ይልቃል ከፋለ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 29፣ 2014 ( ኤፍ ቢ ሲ) የላሊበላ ቅርስ የሰው ልጆች ሁሉ ሃብት በመሆኑ በጋራ ልንጠብቀውና ልንከባከበው ይገባል ሲሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ገለጹ፡፡

የገና በዓል “ገናን በላሊበላ” በሚል መሪ ሐሳብ ከውጭና ከአገር ቤት በርካታ ታዳሚዎች በተገኙበት በአገር አቀፍ ደረጃ በላሊበላ ከተማ ተከብሯል።

በመርሃ ግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት ርእሰ መስተዳድሩ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ቅርስ የሰው ልጆች ሁሉ ሃብት በመሆኑ ሁላችንም ልንጠብቀውና ልንከባከበው ይገባል ብለዋል።

የላሊበላን የስልጣኔ ጸጋ በአካል በመገኘት እንዲማሩበት፣ እንዲመራመሩበት እንዲሁም እንዲጠብቁት ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

የላሊበላ ታሪክ የኢትዮጵያውያን የስልጣኔና የባህል ጥንታዊነት ማሳያ መሆኑን ጠቅሰው ፥ በጥንት ዘመን ሰዎች የሰሩትን ድንቅ ተግባርና ፈጣሪነት አመላካች መሆኑን አስረድተዋል።

የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት የእምነት ቦታ ብቻ ሳይሆን እጹብ ድንቅ የሆነ የስልጣኔና የባህል መገለጫ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

ላሊበላ የቀጣዩ ትውልድ የእውቀት ፈለግና ብርሃን ፈንጣቂ፤ የእውቀትና የቴክኖሎጂ አሻራ ብቻ ሳይሆን የጽናትና የስነ- ምግባር ተምሳሌት መሆኑን አንስተዋል፡፡

በመሆኑም ይህ የስልጣኔና የጽናት ተምሳሌት የሆነ ቅርስ በሰው ልጆች ሁሉ ሊጠበቅ ይገባል ብለዋል።

በጦርነቱ ምክንያት ሀብት ንብረቶቻቸው ለወደመባቸው ወገኖቻችን ከጎናቸው በመሆን ድጋፍ ልናደርግላቸው ይገባል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በደረሰባቸው ጥቃት ክፉኛ ላዘኑና ለተጎዱ ወገኖቻችን ይህ የገና በዓል ልባቸውን ይጠግናል ብለዋል።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.