Fana: At a Speed of Life!

የሕዳሴው ግድብ የሱዳን ህዝብን ተጠቃሚ የሚያደርግ ትልቅ ፕሮጀክት ነው — የሱዳን ባለሀብቶች ልዑካን ቡድን መሪ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 17፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሱዳን ህዝብን ተጠቃሚ የሚያደርግ ትልቅ ፕሮጀክት ነው ሲሉ የሱዳን ባለሀብቶች የልዑካን ቡድን መሪ ታግለዲን አብዱልጃሲም ተናገሩ።

የሱዳን ባለሀብቶችም የልዑካን ቡድን ከመስከረም 12 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ ጉብኝት በማድረግ ላይ ይገኛሉ።

በጉብኝታቸውም የልዑካን ቡድኑ መሪ ታግለዲን አብዱልጃሲም የሕዳሴ ግድብ ሱዳንን ተጠቃሚ የሚያደርግ ትልቅ ፕሮጀክት መሆኑን ነው የገለጹት።

የሕዳሴው ግድብ የሁለቱን አገራት ህዝቦች በልማት የማስተሳሰር አቅም ያለውና የሁለትዮሽ ትብብርን የሚያጠናክር መሆኑንም ገልጸዋል።

ሁለቱ አገራት በደም የተሳሰረ ግንኙነት እንዳላቸውም ነው ሚስተር ታግለዲን ያመለከቱት።

የልዑካን ቡድኑ መሪ ታግለዲን ሁለቱ አገራት በንግድና ኢንቨስትመንት ያላቸውን ትብብር አሁን ካለበት ደረጃ ከፍ ማድረግ ይገባቸዋል ሲሉ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያና ሱዳን ከቱሪዝም ዘርፉ በተጨማሪ በጤናና በሌሎች መስኮች ትብብር በመፍጠር ግንኙነታቸውን ማጎልበት የሚችሉባቸው አማራጮች እንዳሉም መጠቆማቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በራስ አቅም እየተገነባ ያለው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አጠቃላይ የግንባታው አፈጻጸም ከ75 በመቶ በላይ የደረሰ ሲሆን ግንባታውም በ2015 ዓ.ም ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.