Fana: At a Speed of Life!

የሰዎች ለሰዎች ድርጅት ለልማት ስራዎች 600 ሚሊየን ብር በጀት መድቦ እየተንቀሳቀሰ ነው

አዲስ አበባ፣ የካቲት 9፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የሰዎች ለሰዎች ድርጅት በ2013/2014 በጀት ዓመት በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ለሚያከናውናቸው የልማት ስራዎችን ለማከናወን የ600 ሚሊየን ብር በጀት መድቦ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ገለፀ።

ድርጅቱ የጤና ሚኒስቴር ኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል የሚያደርገውን ጥረት ለማገዝ ከ102 ሺህ ዩሮ በላይ ወጪ የተደረገባቸው የሕክምና ቁሳቁስ ለመለገስ መዘጋጀቱን ገልጿል።

የድርጅቱ የኢትዮጵያ ተጠሪ አቶ ይልማ ታዬ እንዳሉት፤ በጀቱ ለግብርናና ተፈጥሮ ሃብትና ለውሃ ልማት፣ ለትምህርት፣ ለጤና፣ ለቤተሰብ ምጣኔ፣ ለኤች.አይ.ቪ/ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር፣ ለሰው ሃብት ልማት፣ ለስራ ዕድል ፈጠራና ለተቀናጀ የገጠር መሰረተ ልማት ግንባታ ይውላልም ነው የተባለው።

በዚህም በተቀናጁ የገጠር ልማት ስራዎች ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ፕሮጀክቶች ተቀርጸው እንደሚከናወኑ አስታውቀዋል።

የድርጅቱ የቦርድ ዳይሬክቶሬት አባል ዶክተር ሳባስቲያን ብራንዲስ በበጀት ዓመቱ ከ25ሺህ 200 በላይ ተማሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስምንት አዳዲስ ትምህርት ቤቶች ለመስራትና ግንባታቸው የተጀመሩ 20 ትምህርት ቤቶችን ለማጠናቀቅ መታቀዱን ተናግረዋል።

ድርጅቱ ለወጣቶች የስራ ዕድል ለመፍጠር ማቀዱንና ከ90 ሺህ በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የውሃ ስራዎችን እንደሚያከናውን ተገልጿል።

የጤናውን ዘርፍ ለመደገፍ ለ38ሺህ ህጻናትና ለ129ሺህ ሴቶች በወረዳ ደረጃ በሽታ ተከላካይ የክትባት አገልግሎት እንዲያገኙም ይደረጋል።

በቤተሰብ ምጣኔና ስነ-ተዋልዶ ከ137ሺህ በላይ ሴቶችን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ለማድረግ አስፈላጊው የገንዘብና ቁሳቁስ ድጋፍ እንደሚደረግ ተነግሯል።

በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን አንኮበር ወረዳ በ24 ቀበሌዎችና በኦሮሚያ ምዕራብ ሸዋ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የተቀናጀ የገጠር ልማት ስራዎች እንደሚከናወኑም ተመላክቷል።

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን አምስት ወረዳዎች ለሚገኙ አርሶ አደሮች ሰፊ የቡና ልማት ፕሮጀክት በመቅረፅ ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉንም ኢዜአ ዘግቧል።

እ.አ.አ. 1980 በዶክተር ካርል ሄንዝ የተመሰረተው የሰዎች ለሰዎች ግብረ ሰናይ ድርጅት በኢትዮጵያ ለ40 ዓመታት ሠብዓዊ ተግባራት እያከናወነ የሚገኝ ዓለምዓቀፍ ድርጅት ነው።

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፦ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ዩቲዩብ ቻናል፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.