Fana: At a Speed of Life!

የሰፋፊ እርሻ ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴን ለማሻሻል የባለድርሻ አካላት ምክክር ተካሄደ

አዲስ አበባ ፣መስከረም 6 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የሰፋፊ እርሻ ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴን ለማሻሻል የባለድርሻ አካላት ምክክር በአዳማ ከተማ ተካሂዷል።

በምክክር መድረኩ የሰፋፊ እርሻ ኢንቨስትመንት የሁለተኛ ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን አፈጻጸም ስኬትና ተግዳሮቶች ላይ ውይይት በማድረግ ለቀጣይ አስር ዓመት ዕቅድ ግብዓት የሚሰጥ መሆኑ ተገልጿል።

በምክክር መድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ማንደፍሮ ንጉሴ ÷ ከሰፋፊ እርሻ ኢንቨስትመንት አንጻር ባለፉት አምስት ዓመታት የተሰሩ ስራዎችና ያልተሰሩ ስራዎችን በመለየት አፈጻጸሙ ምን እንደሚመስል በመገምገም እና ቀጣይ 10 ዓመት ዕቅድ የተሻለ እንዲሆን የእያንዳንዱ ባለድርሻ አካላት ሚና ከፍተኛ መሆኑን አንስተዋል።

በመሆኑም በውይይቱ ግብዓት የሚሆኑ ሀሳቦች የሚቀርቡበት ከመሆኑም ባለፈ በ2013 ወደ ተግባር በመቀየር ወደ ስራ መግባት የሚያስችል መርሃ ግብር የሚወጣበት መሆን አለበት ብለዋል።

በምክክር መድረኩ ከእርሻ ኢንቨስትመንት ድጋፍ ዳይሬክቶሬት እና ከሀገር አቀፍ የባለሀብቶች ማህበር በኩል በሰፋፊ እርሻ ኢንቨስትመንት የልማት እንቅስቃሴ የተገኙ ስኬቶችና ልማቱ በዕቅዱ መሠረት ተሰርቶ ለሀገር ኢኮኖሚ ተገቢ አስተዋጽኦ እንዳያበረክት ማነቆች የሆኑ ጉዳዮች ተለይቶ በመንግስት በኩል ትኩረት ተሰጥቶ እንዲሰራበት የሚያመላክት ሪፖርት ቀርቦ ሰፊ ውይይት ተደርጓል፡፡

ችግሮቹም የግብዓት አቅርቦት፣ በቂ መሠረተ ልማት ዝርጋታ አለመኖር፣ የፋይናንስ አቅርቦት ውስንነትና ፍትሃዊነት ችግር፣ የሚሰራና የማይሰራ ባለሀብት ለይቶ ድጋፍ አለመስጠት እና በአንዳንድ አካባቢዎች የፀጥታ ችግሮች መከሰት መሆናቸው ተነስቷል፡፡

የፌደራልና የክልል መንግስታት በቅንጅትና በተናበበ መልኩ በመስራትና ክትትልና ድጋፍ በማጠናከር እነዚህንና ሌሎች ተያያዥ ችግሮችን በመፍታት ሰፋፊ እርሻ ኢንቨስትመንት በዕቅዱ መሠረት እንዲሰራ ለማድረግ ርብርብ ሊያደርጉ ይገባል ተብሏል፡፡

በምክክር መድረኩ የተገኙት የጀርመን አለምአቀፍ ልማት ተራድኦ ድርጅት ተወካይ ድርጅቱ የኢትዮጵያን የሰፋፊ እርሻ ኢንቨስትመንት ልማት እንዲጠናከር የመንግስትንም ሆነ የግል ባለሀብቶች አቅም ለማሳደግ በተቋማት አቅም ግንባታ፣ በቴክኖሎጂና በፋይናንስ አቅርቦት ለመደገፍና ለማብቃት እና በፖሊሲ ዝግጅት ለማገዝ መዘጋጀቱን መናገራቸውን ከግብርና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.