Fana: At a Speed of Life!

የስፖርት አበረታች ቅመሞችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ

አዲስ አበባ  ፣ ሐምሌ 23  ፣2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ጽህፈት ቤት የስፖርት አበረታች ቅመሞችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችል ስምምነት  ተፈራረመ ፡፡

ስምምነቱ የተፈረመው የኢትዮጲያ ብሔራዊ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ጽህፈት ቤት ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ስፖርት ኮሚሽን እና ከአዲስ አበባ ከተማ ስፖርት ኮሚሽን ጋር  ሲሆን÷ የስምምነቱ ዋና ዓላማ በአገር አቀፍ ደረጃ ዶፒንግን ለመከላከልና ለመቆጣጠር   በጋራ ለመንቀሳቀስ እንደሆነ ታውቋል፡፡

ከዚያም ባለፈ የዶፒንግ የህግ ጥሰቶችን በወንጀል ህጉ አንቀጽ 526 ላይ የተደነገገውን ተግባራዊ ለማድረግና በቀጣይ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅባቸውን የክትትልና ቁጥጥር ስራ  በየእርከኑ አጠናክሮ ለማስቀጠል ያስችላል ተብሏል ፡፡

በፕሮግራሙ ላይ የተገኙት የኢፌዲሪ  ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ኤሊያስ ሽኩር ÷ የስፖርት አበረታች ቅመሞችን በጋራ መከላከል ካልተቻለ በሀገራችን መልካም ገፅታ እና በአጠቃላይ በሀገራችን ስፖርት ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ከፍተኛ በመሆኑ ሁሉም የስፖርት ቤተሰብ በቅንጅት ሊሰራ ይገባል ብለዋል ፡፡

ኮሚሽኑም ስፖርቱን በበላይነት እንደሚመራ አካል የስፖርት አበረታች ቅመሞችን የመከላከል ተግባር በ10 ዓመቱ መሪ ዕቅድ ውስጥ እንዲካተት በማድረግ እየተሰራበት ይገኛልም ነው ያሉት ፡፡

በውድድር የሚሳተፉ ስፖርተኞችም የቀደምት አትሌቶችን ፈለግ በመከተል በአሠልጣኞቻቸው የሚሰጣቸውን ስልጠና በመቀበል እና የተፈጥሮ አቅማቸውን በመጠቀም ስፖርቱን ሊከውኑ እንደሚገባ አሳስበዋል ፡፡

የጽህፈት ቤቱ ዋና ዳሬክተር አቶ መኮንን ይደርሳል በበኩላቸው÷ ጽህፈት ቤቱ አበረታች ቅመሞችን በመከላከልና በመቆጣጠር ንጹህ ስፖርት ለማስፋፋት እና የአገራችንንም መልካም ገፅታ ለማስቀጠል በየደረጃው ሰፊ እንቅስቃሴ በመደረግ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም የክትትል እና የምርመራ ተግባር ተዘርግቶ አበረታች ውጤት ማስመዝገብ እንደተቻለ አብራርተዋል፡፡

አያይዘውም ውጤታማ የሆነ የክትትል እና የምርመራ ተግባራትን ለማከናወን መሰል ስምምነቶች ከሁሉም ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች ጋር እንደሚካሄድ ጠቁመው÷ በአሁኑ ሰዓት ከሁለቱ ክልሎች ጋር የተፈረመው ስምምነት  በአዲስ አበባ እና በኦሮሚያ በተለይም በሱልልታ ፣ ሰንዳፋ እና ለገጣፎ ስጋቱ ከፍተኛ በመሆኑ ነው ብለዋል ፡፡

የጽህፈት ቤቱ  ምክትል ዋና ዳሬክተር ወይዘሮ ፋንታዬ ገዛህኝ የክትትል እና የምርመራ የስምምነት ሰንድ አስመልክተው ገለፃ ያድርጉ ሲሆን÷ የስምምነቱ ዓላማ ፣ የሚመራባቸው መርሆችና ህጎች ፣ አወቃቀሩን ከፌደራልና  ከክልል ስፖርት ኮሚሽኖች በሚጠበቁ  ተግባራት ዙሪያ እና የህግ ጥሰት ተጠያቂነት አስመልክተው ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ስፖርት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ዳዊት ይፍሩ እና የኦሮሚያ ክልል ስፖርት ኮሚሽንን ወክለው የተገኙት አቶ መኮንን በቀለ በስምምነቱ  መሰረት ወንጀሉን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የበኩላቸውን እንደሚወጡ  መናገራቸውን ከኢፌዲሪ ስፖርት ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.