Fana: At a Speed of Life!

የበረሃ አንበጣ ጥቃት እንዳይስፋፋና የረሀብ አደጋ እንዳይከሰት ሥራዎች እየተሰሩ ነው -ጠ/ሚ ዐቢይ

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 9 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዛሬ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ የበረሃ አንበጣ ጥቃት እንዳይስፋፋና የረሀብ አደጋ እንዳይከሰት ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን አንስተዋል።
ዘንድሮ ካጋጠመው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በተጨማሪ አንበጣና ጎርፍ ተፈጥሯዊ ተግዳሮት መከሰቱን አውስተዋል።
አንበጣ ከአንድ እስከ አምስት ደረጃዎች እንዳሉት ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፈው ደረጃ ሶስት የነበረውን የአንበጣ መንጋ በአፋር ክልል ከፍተኛ ጉዳት ሳያደርስ መከላከል መቻሉን ጠቁመዋል፡፡
ይሁን እንጅ ደረጃ አምስት የሆነ የበረሃ አንበጣ ከቀይ ባህር አካባቢ በከፍተኛ ሁኔታ ወደ ኢትዮጵያ በመግባት ጉዳት ማድረሱን ተናግረዋል።
በዚህም በከፊል አማራ፣ ኦሮሚያ፣ ትግራይ፣ አፋር እና ሶማሌ በሚገኙ ወረዳዎች ላይ የበረሀ አንበጣ ጉዳት ማድረሱን ገልጸዋል።
በግብርና ሚኒስቴር የተመራ ቡድን በመጀመሪያው ዙር ሊያደርስ የሚችለውን ጉዳት ለመከላከል ሥራ ያከናወነ ቢሆንም በሁለተኛው ዙር የተከሰተው የበረህ አንበጣ ጉዳት ማስከተሉን አንስተዋል።
በእነዚህ አካባቢዎች አራት ሚሊየን ሄክታር መሬት የታረሰ ሲሆን÷ ከዚህ ውስጥ 420 ሺህ ሄክታር የሚሆነው መሬት በአንበጣ መንጋው ጥቃት ደርሶበታል ነው ያሉት።
ለቅኝት የሚሆኑ ሄሊኮፕተሮች እና ድሮኖች እንዲገቡ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠሉንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመው÷ ቅኝት የሚያካሂዱ ሄሊኮፕተሮች ሃገር ውስጥ ከገቡ በኋላ የሚገጣጠሙ መሆኑ ጊዜ ፈጅቷል ብለዋል።
መንግስትም ጉዳቱን ለመቀነስ የአውሮፕላን ርጭት እያደረገ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስፈላጊ ድጋፍ እንደሚያደርግም ነው ያስረዱት፡፡
ከኬሚካል ርጭት ባለፈ አንበጣውን ለማስወገድ በእጅ የማጥፋት ሥራን ስለሚጠይቅ ማኅበረሰቡ ጥረቱን አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።
አሁን ላይ በአንበጣ መንጋው የደረሰው ጉዳት ምርታማነትን ከአምስት በመቶ በላይ እንዳይጎዳ መቆጣጠር ይቻላልም ብለዋል በምላሻቸው።
በዘላቂነት ችግሩን ለመፍታት ደግሞ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ትናንሽ አውሮፕላኖችን የመጠቀም አቅሙን እንዲያጠናክር እየተሠራ መሆኑን አውስተዋል።
ከትምህርት ጋር በተያያዘም በኢትዮጵያ 30 ሚሊየን ተማሪዎች እንዳሉ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ÷ ዘንድሮ ኮሮናን በመከላከል ማስተማር ይገባል ብለዋል።
በዚህም ኮሮናን እየተከላከሉ ትምህርት ለማስቀጠል ከ60 ሺህ በላይ የመማሪያ ክፍሎች መሰራታቸውን አንስተዋል።
በተጨማሪም የትምህርት ሚኒስቴር ለተማሪዎች የአፍ እና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብሎችን ማዘጋጀቱን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
የኮቪድ -19 ወረርሽኝን ለመከላከልም የጤና ሚኒስቴር ያወጣውን መመሪያ መተግበር ተገቢ እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሳስበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ ከለውጡ በኋላ አብዛኛዎቹ ሠላም አስከባሪ ተቋማት የተፈተኑበትና መዋቅራዊ ለውጥም የተደረገባቸው መሆኑንም ነው የገለጹት።
የሃገር መከላከያና የፌደራል ፖሊስ በዕውቀት ላይ የተመሰረት አደረጃጀት መፍጠራቸውንና በስልጠናና በሁኔታ ትንተናም አቅማቸውን ማደራጀታቸውን አብራርተዋል።
በዚህም ተቋማቱ ኢትዮጵያን ከየትኛውም ጠላት የመከላከል ብቃት መፍጠራቸውንም አስረድተዋል።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚፈጠሩ ግጭቶች ከሕዳሴው ግድብ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አላቸውም ነው ያሉት።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.