Fana: At a Speed of Life!

የትምህርት ዘርፍ አመራሮች፣ ሠራተኞችና የግል ኮሌጆች ለመከላከያ ከ29 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ አደረጉ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 27፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የትምህርት ዘርፍ አመራሮች ፣ ሠራተኞችና የግል ኮሌጆች ለአገር መከላከያ ሚኒስቴር ከ29 ሚሊየን ብር በላይ የገንዘብና የዓይነት ድጋፍ አደረገ።

የገንዘብና የዓይነት ድጋፉ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱና ተጠሪ ተቋማቱ ሰራተኞችና አመራሮች ለጀግናው የአገር መከላከያ ሠራዊት እንዲውል የተሰባሰበ እንደሆነ ተገልጿል።

የትምህርት ሚኒስቴር ደኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ ድጋፉን ባስረከቡበት ወቅት እንዳሉት ፥ ትምህርት ሚኒስቴርና ሁለቱ ተጠሪ ተቋማቱ ድጋፉን ያደረጉት በጀግናው የአገር መከላከያ ሰራዊት እየተከፈለ ላለው ዋጋ እውቅና ለመስጠት ነው።

ከቅርብም ከውጪም ጥቅማቸው የተነካባቸው ኃይሎች በኢትዮጵያ ላይ የከፈቱትን ጥቃት በመመከት ላይ ለሚገኘው ጀግናው የአገር መከላከያ ሰራዊት ትምህርት ሚኒስቴር እያደረገ ያለው ድጋፍ ለወደፊቱም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

ድጋፉን የተረከቡት የመከላከያ ሚኒስቴር ዴኤታ ወይዘሮ ማርታ ሉዊጅ በበኩላቸው፥ የትምህርት ሚኒስቴር ላደረገው የገንዘብና የዓይነት ድጋፍ አመስግነው ሠራተኞቹ በሞራል፣ በገንዘብ ፣ በቁሳቁስና በደጀንነት እያደረጉት ያለው ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

የትምህርት ስርዓቱ አገሩን የሚወድ የአገሩን ህልውና የሚያስከብር ለአገሩ አንድነት የሚሰዋ ዜጋ በማፍራት ያለበትን ኃላፊነት አጠናክሮ እንዲወጣም አሳስበዋል።

ለሰራዊቱ ከተደረገው ድጋፍ ውስጥ 29 ሚሊየን 179 ሺህ በላይ ብር በጥሬ ገንዘብ ሲሆን ፥ ቀሪው ለሠራዊቱ ስንቅ የሚሆን የአይነት ድጋፎች መሆናቸው ተገልጿል።

የትምህርት ሚኒስቴርና የተጠሪ ተቋማቱ ሠራተኞችና አመራሮች ከዚህ ቀደምም ለአገር መከላከያ ሠራዊት በገንዘብና በዓይነት ድጋፍ ማድረጋቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.