Fana: At a Speed of Life!

ንጹሐን ዜጎች ዒላማ ሳይሆኑ፣ ከተሞችንና ቅርሶች ሳይጎዱ መቀሌ ለመግባት ተችሏል- ጠ/ሚ ዐቢይ  

አዲስ አበባ፣ ህዳር 19፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ንጹሐን ዜጎች ዒላማ ሳይሆኑ፣ ከተሞችንና ቅርሶች ሳይጎዱ መቀሌ ለመግባት መግባት መቻሉን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ገለፁ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በፌስቡክ ገፃቸው ባስተላለፉት መልእክት፥ የትግራይ ሕዝብ ከስግብግቡ ጁንታ ጋር እንዳልሆነ በተግባር ማስመስከሩን ገልፀዋል።

የመከላከያ ሠራዊት በድል በገሠገሠባቸው የትግራይ አካባቢዎች ሁሉ የትግራይ ሕዝብ ለሀገሩ ያለውን ፍቅርና ለመከላከያ ሠራዊቱ ያለውን ክብር አሳይቷል ብለዋል።

ጁንታው ካስታጠቃቸው ጥቂት የክፋት ኃይሎች ውጭ ያለው የትግራይ ሕዝብ መቀሌ እስኪገባ ድረስ ለመከላከያ ሠራዊቱ የሚጠበቅበትን ድጋፍ ሁሉ አድርጓል፤ ይህም የሠራዊቱን ድልና የጁንታውን ሽንፈት አፋጥኖታል ሲሉም ገልፀዋል።

ስግብግቡ ጁንታ በየትኛውም መመዘኛ ለትግራይ ሕዝብ አይመጥነውም፤ የትግራይ ሕዝብ ከእውነት ጋር በመቆምና የጁንታውን እኩይ ዓላማ በመፃረር ከቀበሌ ቀበሌ፣ ከዞን ዞን መቀሌ እስኪገባ ድረስ ተመሳሳይ ድጋፍ ለሠራዊቱ ሰጥቷል።

“ለዚህም ከፍ ያለ ምስጋናዬን አቀርባለሁ” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፥ ጁንታው በሸሸበት ከተማና አካባቢ ሁሉ የጤና ተቋማትን፣ ትምህርት ቤቶችን፣ ድልድዮችን፣ መንገዶችን፣ መሥሪያ ቤቶችን እያወደመ ሄዷል፤ በዚህም የገዛ ወገኑ  ጠላት መሆኑን አሳይቷል ብለዋል።

“ጁንታው እኔ ከሞትኩ ብሎ ያፈረሳቸውን መሠረተ ልማቶች በፍጥነት በመገንባት የትግራይ ሕዝብ ወደ ሰላማዊ ኑሮው እንዲመለስ ለማድረግ የቻልነውን ሁሉ እንደምናደርግ ቃል እገባለሁ” ሲሉም ገልፀዋል።

“በዚህ ዘመቻችን ንጹሐን ዜጎች ዒላማ ሳይሆኑ፣ ከተሞቻችንና ቅርሶቻችን ሳይጎዱ መቀሌ ለመግባት ተችሏል” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.