Fana: At a Speed of Life!

የአማራ ክልል በኦሮሚያ ክልል በተፈጠረው ችግርና በተፈጥሮ ጉዳዮች ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች ድጋፍ አደረገ

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 8፣ 2012(ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልል በኦሮሚያ ክልል በተፈጠረው ችግር እና በተፈጥሮ ጉዳዮች ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች ድጋፍ አደረገ።

የአሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ እና የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ በዚህ ወቅት የአማራ ክልል በቅርቡ በተፈጠረው የፀጥታ ችግር እና በጎርፍ አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች ላበረከተው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

የአማራ እና የኦሮሞ ህዝቦች ግንኙነት ከስርዓቶች፣ ከመሪዎች እና ከዚያም በላይ የቆዩ የተጋመዱ ህዝቦች ናቸው ብለዋል።

ሁለቱ ህዝቦች የችግር፣ የከፍታ እና የዝቅታ ጊዜያትን አብረው ያሳለፉ መሆናቸውንም ነው የገለፁት።

በሀገሪቱ ከነበሩ ጭቆናዎች እራሳቸውንም ሆነ ሌሎችን የኢትዮጵያ ህዝቦች ለማዳን መስዋዕትነት ከፍለዋል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ብቃት ያለው አመራር በመስጠትም ለውጡ በዚህ ደረጃ እንዲደርስ አድርገዋል ብለዋል።

ሁለቱ ህዝቦች ባለፉት ዓመታት በየክልሎቹ የነበሩ ችግሮችን እና ፈተናዎችን በመደጋገፍ እና በመተባበር ማሳለፋቸውንም አንስተዋል።

አሁን ላይ ሀገሪቱ በውስጥም ሆነ በውጭ የሚያጋጥማትን ፈተና በመቋቋም የሀገሪቱን ሉዓላዊነት እና አንድነት ለመጠበቅ በጋራ እየተሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ከተሰማበት ጊዜ ጀምሮ የአማራ ክልል መንግስት በመደገፍ እና በማፅናናት አብሮነቱን አሳይቷልም ሲሉ ገልፀዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ ፈተናዎች ወደ ፊትም አይቀሩም ያሉ ሲሆን ፈተናዎቹን መቋቋም የሚቻለው በመተጋጋዝ እና በመተባበር እና ያሉትን ችግሮች ነቅሶ በማውጣት አብሮ በመታገል ብቻ መሆኑንም አስረድተዋል።

ለዚህም ሁለቱ ህዝቦች ሃላፊነት አለባቸው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ እነዚህ ህዝቦች ሃላፊነታቸውን ካልተወጡ የምንፈልጋት ኢትዮጵያ እና ሀገር እውን ልትሆን አትችልምም ነው ያሉት።

ሁለቱ ህዝቦች እና ክልሎች ሀላፊነታቸውን ከተወጡ ማንኛውንም ጋሬጣ እና ፈተና በመቋቋም በሚያስፈልገው ቦታ መድረስ ይቻላልም ብለዋል።

በክልሉ ተፈናቅለው የነበሩ 2 ሚሊየን የሚሆኑ ህዝቦችን መልሶ የማቋቋም ስራ መከናወኑ የተገለፀ ሲሆን በዚህም የተቃጠሉ ቤቶችን የመገንባት እና ዘር የማቅረብ ስራም ተከናውኗል ተብሏል።

እንዳንድ ችግሮች ሲታዩም አመራሮችን ተጠያቂ የማድረግ ስራ እየተከናወነ መሆኑን አውስተዋል።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ በበኩላቸው የአማራ ክልል ምግብ ነክ ቁሳቁሶችን እና በአማራ ልማት በኩል የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን በመግለፅ ከዚህ በላይ ተጎጅዎች ወደ ቀያቸው እና ወደ ተመለደው የህይወት ዘይቤያቸው እስከሚመለሱ ድጋፉ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

ለዚህም ከኦሮሚያ ክልል መንግስት ጋር በትብብር እንደሚሰራም ነው የተናገሩት።

በክልሉ የህግ የበላይነትን ለማስከበር እየተሰራ የሚገኘውን ስራ እንደሚያደንቁም ነው ያነሱት።

በተለይ አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ከተገደለ በኋላ የተከናወነው ህግ የማስከበር ስራ ከዚህ የበለጠ ጉዳት ሳይከሰት ያረጋጋ መሆኑንም አስታውሰዋል።

በህግ ጥላ ስር ያለ ሰው ህጋዊ ባልሆነ መንገድ ሳይሆን ህግ እና ስርዓቱ በሚፈቅደው መሰረት ምርመራው ተጣርቶ ጥፋተኞች ተጠያቂ ሲሆኑ ነው ሌላው ህግ እና ስርዓትን እያወቀ የሚሄደው ብለዋል አቶ ተመስገን።

ይህንን ለማድረግም ፖሊስ፣ ዐቃቤ ህግ እና ፍርድ ቤት በሃላፊነታቸው ተባብረው እና ተቀናጅተው በጥፋኞች ላይ ውሳኔ እንዲሰጡም ጠይቀዋል።

በአማራ ክልልም ሆነ በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች ለሚከሰቱ ችግሮች በየአካባቢዎቹ ያሉ አስተዳዳሪዎች ሃላፊነት እንዳለባቸው አጽንኦት ሰጥተዋል።

ኢትዮጵያን ማሳደግ እና መገንባት የሚቻለው ሁሉም ብሄር ብሄረሰብ በትብብር እና በመደጋገፍ ሲሰሩ ነው እንጂ እርስ በእርስ በመፈራረጅ አይደለም ነው ያሉት።

በቅርቡ የተፈፀመውን አይነት ጥቃት በመፈፀም ሀገር ማፍረስ አይቻልም ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ይህን ተግባር የሚፈፅሙ አካላትም ከድርጊታቸው ሊታቀቡ ይገባል ብለዋል።

በእንዲዚህ አይነት ድርጊት የተሰማሩ አካላትም የሁለቱን ህዝቦች አንድነት እና በጋራ የመስራት እቅድና ተስፋ ሊያደናቅፈው አይገባም በማለት ተናግረዋል።

በኤፍሬም ምትኩ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.