Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን የ10 ዓመት መሪ እቅዱ ላይ ውይይት አካሄደ

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 14 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ)የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን የ10 ዓመት መሪ እቅዱ ላይ ውይይት አካሄደ።

ባለስልጣኑ በመሪ እቅዱ የመገናኛ ብዙሃንን ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር መክሯል።

በውይይቱ ላይ የመገናኛ ብዙሃን አሁን ካለው የፖለቲካ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች አንጻር በምን መልኩ መሻሻል አለባቸው የሚሉ ጉዳዮች ተነስተዋል።

የብሮድካስት ባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጌታቸው ድንቁ÷ ለህብረተሰቡ የሚመጥን ሁሉን አቀፍ ሚዲያን ከማጠናከር እና ተደራሽነታቸውን ከማስፋት አንጻር የ10 ዓመቱ መሪ እቅድ ማዘጋጀት ማስፈለጉን ተናግረዋል።

በዚህም የመገናኛ ብዙሃን አስተካካይና አራሚ፣አዝናኝና አስተማሪ እንዲሁም ነቃሽና ጠቋሚ ይሆኑ ዘንድ ማጠናከር የመሪ እቅዱ ትኩረት መሆኑን አንስተዋል ።

ከዚያም ባለፈ የመገናኛ ብዙሃንን የየክትትል ስራ ማስፋት፣የማስታወቂያ ዘርፉን የክትትል ስራ ማጠናከርና ማስፋት የጥናት አቅምን ማሳደግ የመሪ እቅዱ የትኩረት አቅጣጫዎች ናቸው ብለዋል።

ከዚህም አንጻር በቀጣይ 10 ዓመት ውስጥ አሁን ካለው የግል የሬዲዮ ጣቢያዎች ተጨማሪ አንድ መቶ ለሚሆኑ ፈቃድ የሚሰጥ ሲሆን÷ ለማህበረሰብ የሬድዮ ጣቢያዎችም ተጨማሪ አንድ መቶ ፈቃድ ይሰጣል ብለዋል።

ከዚያም ባለፈ አሁን ካሉት የሳተላይት የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ተጨማሪ 70 አዳዲስ ፈቃዶች ይሰጣልም ነው ያሉት ።

ሃላፊው አያይዘውም ባለስልጣኝ መስሪያ ቤቱ በቅርቡ የጸደቀውን የመገናኛ ብዙሃን ፖሊሲን ተከትሎ አንድ መገናኛ ብዙሃን አራቱንም ማለትም የሬድዮ፣የቴሌቪዥን ፣የጋዜጣና መጽሄት አውታሮችን መጠቀም ይችላል ብለዋል።

ከዚያም ባለፈ በአዲሱ ፖሊሲ ለሀይማኖት ተቋማት እና ለትውልደ ኢትዮጵያውያን የቴሌቪዥን ፈቃድ የሚሰጥ ሲሆን ለመገናኛ ብዙሃን የሚገቡ መሳሪያዎች ላይ የሚጣለው ቀረጥ ቅናሽ እንደሚደረግ ተናግረዋል።

የመሪ እቅዱ ውይይት የመገናኛ ብዙህን ሃላፊዎች፣የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ፣የፍትህና ዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት ፣ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት እንዲሁም የባለስልጣኑ ቦርድ አመራሮች በተገኙበት ነው የተካሄደው።

በጸጋዬ ንጉስ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.