Fana: At a Speed of Life!

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ከቻይና አምባሳደር ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 17፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ)የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር አብርሐም በላይ ከቻይና አምባሳደር ዥአኦ ዢህሁ ጋር በጽህፈት ቤታቸው ተወያይተዋል።

ሚኒስትሩ የኢትዮ ቻይናን በይነ መንግስታዊ እና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትና ትብብርን ለማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች በተለይም በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ዘርፎች ላይ ከአምባሳደሩ ጋር ተወያይተዋል።

ኢትዮጵያና ቻይና ረጅም ዘመንን የተሻገረ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትና ታሪክ ያላቸው መሆኑን የገለጹት ዶክተር አብርሃም፣ የአገራቱ ግንኙነት በሁለትዮሽ የጋራ ተጠቃሚነትና ስትራቴጂካዊ ጉዳዮች ላይ ተመስርቶ ተጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል።

እንደ ዶክተር አብርሐም ዘመን ተሻጋሪ የሆነውን የሁለቱ አገራት ትብብርና ግንኙነት ዘላቂና የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በሚያስችል መልኩ አጠናክሮ ማስቀጠል ይፈለጋል ሲሉ ለአምባሳደሩ አስገንዝበዋል።

የሁለቱ አገራት ግንኙነት ተጠናክሮ በመቀጠሉ የቻይና ሕዝብና መንግስት ከህዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ባሻገር ኢትዮጵያ ወደ ሕዋ ለምታደርገው ጥረት ከቻይና በተገኘው ድጋፍ የመጀመሪያውን ሳተላይት ማምጠቅ ሂደትም ላይ መሰረት መጣላቸውን በማውሳት ለተደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

የቻይናው አምባሳደር በበኩላቸው አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር የነበራትን የብዙ ዓመታት ግንኙነት በማጠናከር ዘላቂና ቀጣይ ማድረግ ይፈለጋል ብለዋል።

ይህን ዘመን የተሻገረ የሁለትዮሽ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ የተጀመሩ ድጋፎችን፤ በስፔስ ቴክኖሎጂ፣ በባህል ሕክምና፣ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማትና የኤሌክትሮኒክ ግብይት፣ በዘመናዊ እና ምቹ የመኖሪያ መንደሮች ልማት እና በአጠቃላይ የቴክኖሎጂ ዘርፍ መንግስታቸው አስፈላጊውን ድጋፍ እናደርጋለን ብለዋል።

አምባሳደሩ አክለውም የቻይና ባለሃብቶች በግሉ ዘርፍ ከኢትዮጵያውያን ጋር በትብብር መስራት እንዲችሉ ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር አሳስበዋል።

ከተሞችን ውብና ምቹ ለማረግ በጠቅላይ ሚኒስትር የተጀመረውን ጥረትና መነሳሳት ለመደገፍ ከአረንጓዴ ልማት ጋር ተሳስሮ እንዲተገበር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ በመርህ ደረጃ መግባባት መግባባት ላይ ተደርሷል።

ለአተገባበሩም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አስፈጻሚ ቡድን በማቋቋም ከኤምባሲ አቻቸው ጋር የቀጥታ ግንኙነት ለመጀመር ስምምነት ተደርሷል።

በባህል ሕክምና ዘርፉ ኢትዮጵያ የቻይናን ተግባራዊ ልምድ በማምጣት እና ከአሁን በፊት የተጀመሩ ጥረቶች ጋር በማከል አጠናክሮ ለማስቀጠል ስምምነት ላይ ደርሰዋል።

ሌላው በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ፖሊሲ አገራዊ ማዕቀፍ እይታና አሰራሮች ላይ ኢትዮጵያ ልትወስደው በሚገባት ልምድ በተመለከተ የቻይና መንግስት እገዛ ለማድረግ ፍላጎት እንዳለው ተጠቁሟል።
የሚኒስቴር መስሪያቤቱን አገልግሎቶች ወደ መላ ሕዝቡ ለማድረስ የተጀመረውን ከቢሮ ወደ ሕዝብ የተሰኘ መነሳሳት ለመደገፍ ቀጣይ ምክክር ለማድረግ ስምምነት ተደርሷል።

ሚኒስትሩ ከአምባሳደሩ ጋር በነበራቸው ውይይት የተደረገላቸውን ምላሽ አመስግነው በቀጣይ መወያየት እንዲችሉ በአምባሳደሩ ተጋብዘዋል፡፡

አምባሳደሩ በበኩላቸው በግላቸው ያላቸውን የሃይ ቴክ ልምድና ግንኙነት ኢትዮጵያ ለምታደርገው እንቅስቃሴ ለማዋል ቃል በመግባት አጠቃላይ አተገባበሮችን ለመከታተል የሚያስችል ግንኙነት እንዲዘረጋ የላቀ መግባባት ላይ መደረሱን ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡-

https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.