Fana: At a Speed of Life!

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ ከኬንያና ከሩዋንዳ አቻዎቻቸው ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ጥር 27፣2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሪቼል አውር ኦማሞ ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም ሀገራቱ በሁለትዮሽ እና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ትብብር ማጠናከር በሚችሉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል።

አቶ ገዱ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረ፣ በመተማመን ላይ የተመሰረተ፣ የማይለዋወጥ እና በሁሉም ዘርፍ በምሳሌነት የሚጠቀስ መሆኑን አውስተዋል፡፡

በቀደሞው የኬንያ ፕሬዚዳንት ዳንኤል አራፕ ሞይ ህይወት ማለፍ የተሰማቸውን ሀዘንም ገልጸዋል።
በሀገራቱ መካከል ከዚህ በፊት የተመሰረቱ ስምምነቶችን በማጠናከር እና አዳዲስ የትብብር መስኮችን በመለየት ትስስራቸውን ይበልጥ ማጠናከር እንዳለበቸውም ጠቁመዋል።

የተደረሱ ‘የልዩ ደረጃ ስምምነቶችን” ተግባራዊ በማድረግ በኩል ያጋጠሙ ችግሮችን በመለየት የሀገራቱን ህዝቦች ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፍላጎቶች ለማሳካት መረባረብ ያስፈልጋል ነው ያሉት አቶ ገዱ።

ከሁለትዮሽ ግንኙነት በተጨማሪ በኢጋድ፣ በአፍሪካ ህብረት፣ በተመድ እና በሌሎች ዓለም አቀፍ መድረኮች የሚያደርጉትን ትብብር በየጊዜው እየፈተሹ ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር እንዳለባቸውም አንስተዋል።

የኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሪቼል አውር ኦማሞ በበኩላቸው፥ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ መምጣቱን አብራርተዋል ።

ሁለቱ ሀገራት በአሁኑ ስዓት በቀጠናው ያላቸውን ፖለቲካዊ ትብብር በኢኮኖሚ እና በማህበራዊ ዘርፎች ይበልጥ አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውም አምባሳደር ኦማሞ ገልጸዋል።

ከዚህ ባለፈም በመሰረተ ልማት ለማስተሳሰር እየተከናወነ ያለው ስራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ነው ሚኒስትሩ የተናገሩት።

የሀገራቱን ህዝቦች ኑሮ ለማሻሻል የሚችሉ የጋራ ፕሮጀክቶችን በመለየት በትብብር መስራት እንደሚገባ ማሳሰባቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ምስራቅ አፍሪካን እያጠቃ ያለውን የበረሃ አንበጣ እና ካለወቅቱ በሚጥል ዝናብ የሚከሰትን ጎርፍ ለመከላከል የሚያስችል የጋራ ፕሮጀክት በመቅረጽ በትብብር መስራት እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል።

በሌላም በኩል አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከሩዋንዳ የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ከሆኑት ዶክተር ቪንሰንት ቢሩታ ጋር በሁለቱ አገራት የጋራ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡

አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የሩዋንዳው አቻቸው የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር በመሆን በመሾማቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው÷በሚኒስትርነት ዘመናቸው የሁለቱ አገራት ግንኙነት ይበልጥ እንደሚጠናከር እምነታቸው መሆኑን ገልፀዋል፡፡

አቶ ገዱ ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ በህዳሴው ግድብ ውሃ ሙሊት እና አለቃቀቅ ዙሪያ በቅርቡ ያደረጉትን ውይይት በተመለከተ ገለጻ አድርገዋል።

ዶክተር ቪንሰንት ቢሩታ በበኩላቸው ኢትዮጵያ እና ሩዋንዳ ጠንካራ የሁለትዮሽ ግንኙነት እንዳላቸው በማንሳት ሁለቱ አገራት በሁለትየሽ ፣ በአፍሪካ ህብረት እና በሌሎችም ዓለም አቀፍ መድረኮች በትብብር ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።አቶ ገዱ በሩዋንዳ ጉብኝት እንደያደርጉም ግብዣ አቅርበዋል።

ሚኒስትሮቹ ሁለቱ አገሮች ግንኘነታቸውን ለማጠናከር ይረዳ ዘንድ ያቋቋሙትን የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ በቅርቡ እንዲካሄድ ከስምምነት ላይ መድረሳቸውም ተገልጿል፡፡

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.