Fana: At a Speed of Life!

የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ ፕሬዚዳንት  በጅግጅጋ የሚገኘውን የአካል ጉዳተኞች መልሶ ማቋቋሚያ ማዕከልን ጎበኙ

አዲስ አበባ፣ ጥር 5 ፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ)የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ፒተር ማውራ በአለም አቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ ድጋፍ የሚደረግለትን የአካል ጉዳተኞች መልሶ ማቋቋሚያ ማዕከል ጎበኙ፡፡

ፕሬዚዳንቱ በኢትዮጵያ የሚያደርጉትን ጉብኝት በጅግጅጋ የጀመሩ ሲሆን በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ በአለም አቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ ድጋፍ በሚደረግለት የአካል ጉዳተኞች መልሶ ማቋቋሚያ ማዕከል ቆይታ አድርገዋል፡፡

ማዕከሉ ባለፈው ታህሳስ  ወር  በክልሉ የሚኖሩ የአካል ጉዳተኞችን መልሶ ለማቋቋም እና ለአካል ጉዳተኞች የአገልግሎት አቅርቦትን እንዲያሻሽል በማሰብ የተከፈተ ነው፡፡

ይህ የአካል ጉዳተኞች መልሶ ማቋቋሚያ ማዕከል በመላው አገሪቱ ከሚገኙና በአለም አቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ ድጋፍ ከሚደረግላቸው አስር ማዕከላት መካከል አንደኛው ነው፡፡

በተያያዘ ዜና ፕሬዚዳንቱ በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል ጭናቅሰን ወረዳ ጉብኝት አድርገዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ በአለም አቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ ድጋፍ በጭናቅሰን መሰረታዊ ጤና ጣቢያ የተከናወኑ ስራዎችን ተመልክተዋል፡፡

የጤና ጣቢያው ለእናቶች እና ህጻናት የሚሰጠውን የጤና አገልግሎት ለማሻሻል እንዲረዳ በአለም አቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ የእናቶች እና ህጻናት ጤና መጠበቂያ ቁሳቁስ እና መድሃኒቶች ድጋፍ ተደርጎለታል፡፡

በተጨማሪም ተፈናቃይ፣ ተመላሽ እና የአካባቢው ነዋሪ ለሆኑ 400 እናቶች በጤና ጣቢያው ሲወልዱ ድጋፍ ተደርጓላቸዋል፡፡

እንዲሁም 3 ሺህ 250 ህጻናት በልጅነት በሚያጋጥሙ በሽታዎች እንዳይጠቁ እና ከበሽታ እንዲያገግሙ መድሃኒቶች እንዲሰራጭ መደረጉ ተጠቁሟል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.