Fana: At a Speed of Life!

የዲፕሎማሲ ስራዎችን በማጠናከር ወዳጅነትን ማብዛት ይገባል-ቋሚ ኮሚቴው

አዲስ አበባ፣ ጥር 20፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ጉንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በውጭ ጉዳይ ሚንስቴር የመስክ ምልከታ ባደረገበት ወቅት የተጀመሩት የዲፕሎማሲ ስራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ ጠቁሟል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የሚንስቴር መስሪያ ቤቱን የስድስት ወራት እቅድ አፈጻጸም ለቋሚ ኮሚቴው ባስረዱበት ወቅት÷ የኢትዮጵያን ጥቅም ለማስጠበቅ በአለም አቀፍ እና በአፍሪካ ደረጃ ጠንከር ያለ የዲፕሎማሲ ስራ እየተሰራ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ራስዋን በዲፕሎማሲ መንገድ ለመመከት ወሳኝ ምዕራፍ ላይ በመሆንዋ የሃገሪቱን ገጽታ ለመገንባት ሁሉም ዜጋ የሃገር አምባሳደር መሆን እንዳለበት ጠቁመው÷ሃገሪቱ ካለችበት ነባራዊ ሁኔታ አንጻር የዲያስፖራው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ሚኒስትሩ አመላክተዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ዶክተር ነገሪ ሌንጮ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የተጀመሩ የዲፕሎማሲ ስራዎችን አጠናክሮ በመቀጠል ወዳጅነትን ማብዛት እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ግጭትን እንደ መፍትሄ የሚወስዱ አካላት ወደ ሰላማዊ መንገድ እንዲመለሱ እንዲሁም ሁሉም ዜጋ የሃገር ገጽታ ግንባታ ላይ የራሱን አስተዋጽኦ ማበርከት እንዳለበት ነው ያሳሰቡት፡፡
አያይዘውም ወቅታዊ መረጃዎች በተለያዩ ቋንቋዎች ተደራሽ የሚሆኑበት ሁኔታ እንዲፈጠር ከኤምባሲዎች ጋር ያለ ግንኙነት እና የሚሰጥ ድጋፍ ቀልጣፋ እና ዘመናዊ ሊሆን እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡
በሌላ በኩል ወደተለያዩ ሃገራት ለትምህርት የሚሄዱ ዜጎች በሚሄዱበት አካባቢ የሃገር ገጽታ የመገንባት ስራ በመስራትና ተጽእኖ በመፍጠር ውጤት ሊያስገኙ እንደሚችሉም ነው የገለጹት ፡፡
ቋሚ ኮሚቴው የሚንስቴር መስሪያ ቤቱን የስራ እንቅስቃሴ በየስራ ክፍሉ ተዘዋውሮ የተመለከተ ሲሆን÷ ከተለያዩ አምባሳደሮች እና የቆንጽላ ጀነራሎች ጋር በቴክኖሎጂ በመታገዝ የቪዲዮ ኮንፍረንስ አድርገዋል፡፡
ከዚያም ባለፈ በተቋሙ የሴቶችን አቅም ለመገንባት እና ወደ አመራርነት ለማምጣት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ይመች ዘንድ የተዘጋጀው የህጻናት ማቆያ በቋሚ ኮሚቴው መጎብኘቱን ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.