Fana: At a Speed of Life!

የጭልጋ አካባቢን ወደ መደበኛ እንቅስቃሴ ለመመለስ ያለመ ግብረሀይል ተቋቁሞ ስራ ጀመረ

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 21 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የጭልጋ አካባቢን ወደ መደበኛ እንቅስቃሴ ለመመለስና የአካባቢውን ሰላም አስተማማኝ ለማድረግ ያለመ ግብረሀይል (ኮማንድ ፖስት) ተቋቁሞ ስራ መጀመሩ ተገለፀ።

በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ከሰሞኑ ግጭት በተከሰተበትን የጭልጋ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ  መከላከያና ፓሊስ መግለጫ ሰጥተዋል።

መግለጫውን የሰጡት የኮማንድ ፓስቱ አባል የሆኑት ከ33ኛ ክፍለጦር ሻለቃ ከተማው ብናልፈው እና የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ፓሊስ መምሪያ ሀላፊ ኮማንደር እንየው ዘውዴ አካባቢውን ለማረጋጋትና ፀረሰላም ሀይሎችን ለህግ ለማቅረብ ኮማንድ ፖስት መቋቋሙን ተናግረዋል።

ፀረሰላም ሀይሎች በአይከል ከተማና አካባቢው ባደረሱት ጥፋት ሰብአዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት እንደደረሰ ተገልጿል።

በመግለጫው እንደተጠቀሰው  ከሰሞኑ  በፀረሰላም ሀይሎች የደረሰው ጥፋት ከአሁን በፊት በአካባቢው  ሲያጋጥም ከነበረው የተለየ ዝግጅትና አላማ እንደነበረው የሚያሳዩ ምልክቶች ታይተዋል ብለዋል።

አጠቃላይ የደረሰው ጉዳትና የጥፋት ተዋናዮችን በተመለከተ ምርመራ እየተካሄደ መሆኑ ተነግሯል።

በአካባቢው ተቋርጦ የነበረውን ማህበራዊ አገልግሎት ለማስጀመር  የጎንደር-መተማ-ሱዳን መንገድን አስተማማኝ ለማድረግ ብሎም አጥፊዎችን ከገቡበት ገብቶ ለህግ ለማቅረብ የፌደራልና የክልል የፀጥታ አካላትን እንዲሁም የአስተዳዳር አካላትን ያካተተ ኮማንድ ፖስት ስራ መጀመሩን ሻለቃ ከተማው ተናግረዋል።

ኮማንድ ፖስቱ ከሚመለከታቸው የፌደራልና የክልል ህግ አስከባሪዎች ውጪ –  ከዋናው መንገድ ግራና ቀኝ መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስን፣ ከወረዳ ወረዳና ከቀበሌ ቀበሌ መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስን እንደከለከለ ገልፀዋል።

የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ፖሊስ መምሪያ ሀላፊ ኮማንደር እንየው በበኩላቸው÷ አጥፊዎችን ለህግ ለማቅረብ በሚደረገው ጥረት የአካባቢው ህዝብ አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በህዝብ ስም የተደበቁ ሽፍቶችን የጥፋት አላማ በመገንዘብ የቀጠናውን ሰላም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማረጋገጥ ለሚደረገው ጥረት ህብረተሰቡ የሚጠበቅበትን እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።

በነብዩ ዮሐንስ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.