Fana: At a Speed of Life!

የፖለቲካ ፓርቲዎች የዕጩዎች የድጋፍ ፊርማ የማቅረብ ግዴታቸው እንዲነሳ የውሳኔ ሀሳብ ቀረበ

አዲስ አበባ፣ ጥር 13፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ)ለ6ኛው አገራዊ ምርጫ የፖለቲካ ፓርቲዎች የዕጩዎች የድጋፍ ፊርማ የማቅረብ ግዴታቸው እንዲነሳ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውሳኔ ሀሳብ አቀረበ።

ቦርዱ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ የተጣበበ የምርጫ ሰሌዳ እና የፖለቲካ ፓርቲዎች ተደጋጋሚ ቅሬታ የድጋፍ ፊርማው እንዲነሳ ያደረጉ ምክንያቶች መሆናቸውም ተናግሯል።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በ2013 ዓ.ም በመላ ኢትዮጵያ ለሚያካሄደው ጠቅላላ ምርጫ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ስነ-ምግባር አዋጅ 1162/2011 አንቀጽ 32/2/ መሰረት የፖለቲካ ፓርቲ ዕጩዎች የድጋፍ ፊርማ መቅረብ እንዳለባቸው ይደነግጋል።

ቦርዱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ስነ-ምግባር አዋጅ አንቀጽ 32 በጊዜያዊነት እዲታገድ የውሳኔ ሀሳብ አቅርቧል።

ለዚህ ደግሞ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የምርጫ ወረቀት ልውውጥና ንክኪን ለመቀነስ፣ ባለው የተጣበበ የምርጫ ሰሌዳ ምክንያት ፓርቲዎቹ ፊርማ ለማሰባሰብ በቂ ጊዜ አለማግኘታቸው እንዲሁም አንቀጹ በፖለቲካ ፓርቲዎች ተደጋጋሚ ቅሬታ ያስነሳ መሆኑ በምክንያትነት አንስቷል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 8ኛ መደበኛ ስብሰባ በቦርዱ የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ ለማጽደቅ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ ለዝርዝር እይታ መርቷል።

እንዲሁም የህግ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የፌዴራል የዳኝነት አስተዳደርን እንዲሁም የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ረቂቅ አዋጅን በተመለከተ ያቀረበውን ሪፖርትና የውሳኔ ሀሳብ መርምሮ አጽድቋል።

በሌላ በኩል ምክር ቤቱ የካፒታል ገበያ ረቂቅ አዋጅ ለዝርዝር እይታ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ የመራ ሲሆን፤ መንግስት ከኡጋንዳ ጋር በወንጀል የሚፈለጉ ሰዎችን አሳልፎ ለመስጠትና በወንጀል ጉዳዮች የጋራ የፍትህ ትብብር ስምምነት ለማጽደቅ የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ መርምሮ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መምራቱን ኢዜአ ዘግቧል።

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.