Fana: At a Speed of Life!

የ76 ንጹሃን ዜጎችን ህይወት በአሰቃቂ ሁኔታ እንዲጠፋ ያደረጉ ተከሳሾች እስከ እድሜ ልክ ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ተወሰነባቸው

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመተከል ዞን በማንዱራ፣ ዳንጉር እና ፓዊ ወረዳዎች የ76 ንጹሃን ዜጎችን ህይወት በአሰቃቂ ሁኔታ እንዲጠፋ ያደረጉ ተከሳሾች እንደየወንጀል ተሳትፏቸው ከእድሜ ልክ ጀምሮ በጽኑ እስራት እንዲቀጡ ተወሰነ፡፡

ተከሳሾቹ በተጠቀሱት አካባቢዎች የእርስ እርስ ጦርነት እንዲነሳና ብሔር-ተኮር ግጭት እንዲቀሰቀስ በማድረግ የ76 ንጹሃን ዜጎች ህይወት በአሰቃቂ ሁኔታ እንዲጠፋና ከፍተኛ ንብረት እንዲወድም በማድረጋቸው ነው ከእድሜ ልክ እስከ 8 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እንዲቀጡ የተወሰነባቸው፡፡

በዚህ መሰረትም እነ ፋንቻ አምሳያ በተከሰሱበት መዝገብ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የወንጀል ህግ አንቀጽ 240(1ለ)፤(2)፣ 539(1ሀ) እና 27(1) እና 539(1ሀ) ላይ የተመለከተውን ድንጋጌ በመተላለፍ አንዱ ወገን በሌላዉ ወገን ላይ የጦር መሳሪያ እንዲያነሳ በማነሳሳት የእርስ በእርስ ጦርነት እንዲነሳ በማድረግ በፈጸሙት ወንጀል በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የመተከል ዞን ተዘዋዋሪ ችሎት ቀርበዋል፡፡

ተከሳሾች ዜጎችን ወይም በአገር ነዋሪ የሆኑትን በማሰታጠቅ፣ አንዱ ወገን በሌላዉ ወገን ላይ የጦር መሳሪያ እንዲያነሳ በማነሳሳት የእርስ በእርስ ጦርነት እንዲነሳ በማድረግ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን በማንዱራ፣ ዳንጉር እና ፓዊ ወረዳዎች በ2011 ዓ.ም ከታህሳስ እሰከ ሰኔ ወር አጋማሽ ድረስ ብሔር ተኮር ግጭትን ቀስቅሰዋል፡፡

በዚህም በአጠቃላይ የ76 ንጹሃን ዜጎች ህይወት በአሰቃቂ ሁኔታ እንዲጠፋ፣ በ20 ሰዎች ላይ ከባድ የአካል ጉዳት እንዲደርስ፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ከቤት ንብረታቸዉ እንዲፈናቀሉ በማድረግ እና ግምቱ ከፍተኛ የሆነ ንብረት እንዲዘረፍ እና እንዲወድም በማድረግ የወንጀል ድርጊት ዉስጥ በመሳተፋቸው በፈጸሙት ወንጀል በዓቃቤ ህግ ተከሰዋል፡፡

የፌዴራል ዓቃቤ ህግ የተከሳሾችን ጥፋተኝነት የሚያረጋግጡ ማስረጃዎቹን አቅረቦ ለፍርድ ቤቱ ያሰማ ሲሆን÷ ጉዳያቸውን ሲከታተሉ ከነበሩ 29 ተከሳሾች መካከል 3ቱ የቀረበባቸውን ክስ እና ማስረጃ መከላከል በመቻላቸው በነጻ ተሰናብተዋል፡፡

በ26 ተከሳሾች ላይ ደግሞ የወንጀል ህግ አንቀጽ 240 (1ለ)፤(2) ፣539(1ሀ) እና 27(1) እና 540 አንቀጹ ተቀይሮ እንደየተሳትፏቸው ደረጃ የጥፋተኝነት እና የቅጣት ውሳኔ የተሰጠባቸው መሆኑን ከፍትህ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በመሆኑም የመተከል ዞን ተዘዋዋሪ ችሎት ግንቦት 12 ቀን 2014 ዓ.ም በዋለው ችሎት 4 ተከሳሾች ላይ የእድሜ ልክ ጽኑ እስራት፣ 1 ተከሳሽ በ 25 ዓመት ጽኑ እስራት፣ 1 ተከሳሽ በ 23 ዓመት ጽኑ እስራት፣ 17 ተከሳሾች በ 22 ዓመት ጽኑ እስራት፣ 2 ተከሳሾች በ 20 ዓመት ጽኑ እስራት እና 1 ተከሳሽ ዕድሜው ለአካለ መጠን ያልደረሰ በመሆኑ በልዩ ሁኔታ በ 8 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ እንዲሁም ሁሉም ተከሳሾች ከሲቪል መብቶቻቸው ለ 5 ዓመት ታግደው እንዲቆዩ ውሳኔ ተላልፎባቸዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.