Fana: At a Speed of Life!

ጎንደር፣ ዲላ እና አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲዎች ትምህርት መጀመር ይችላሉ ተባለ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 27፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ጎንደር፣ ዲላ እና አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲዎች የመማር ማስተማሩን ሂደት እንደገና ለማስቀጠል የሚያስችል አቋም ላይ እንደሚገኙ ከሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የተላከው የምርመራ ቡድን አረጋግጧል::

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የኮሮና ቫይረስን ግምት ውስጥ በማስገባት ዩኒቨርሲቲዎች ትምህርት የሚጀምሩበትን ቁመና የሚገመግም ቡድን ወደየተቋማቱ መላኩ ይታወቃል::

በዚህ መሰረት ወደ ጎንደር፣ ዲላ እና አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲዎች የተላኩ የግምገማና ክትትል ቡድኖች ተቋማቱ በጤና ሚኒስቴር የወጣውን የኮሮና ቫይረስ መከላከያ መንገዶች ተግባራዊ በማድረግ ትምህርት የማስጀመር አቋም ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የጎንደር ዩኒቨርሲቲን ዝግጅት የገመገመው ቡድን መሪ አቶ ከበደ ግዛው እና የዲላ ዩኒቨርሲቲ ዝግጅት ለመገምገም የተላከው ቡድን መሪ አቶ ጌታቸው ተፈራ ዩኒቨርሲቲዎቹ ተማሪዎች በግቢዎቹ በሚኖራቸው ቆይታ አካላዊ ርቀታቸውን እና ንጽህናቸው ጠብቀው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ የሚያስችል በቂ ዝግጅት ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡

የመመገቢያ ቤቶችን፣ ቤተ መጻሕፍት፣ ቤተ ሙከራዎችን እና ላውንጆችም የኮሮና ቫይረስ ኬሚካል ርጭት የተደረገባቸው መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡

በተጨማሪም የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል አስተማማኝ የውሃ አቅርቦት እንዲሁም ማስክ እና ሳኒታይዘር መዘጋጀቱንም ተናግረዋል፡፡

ሌሎች ተማሪዎችን ለመቀበል የሚያስፈልጉ መሠረታዊ አገልግሎቶች እንዲሁም የፀጥታ እና ደህንነት ጉዳይም አስፈላጊ ቅድመ ዝግጅት እንደተደረገበትም ተመላክቷል፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ዝግጅት የገመገመው ቡድን መሪ አቶ ጫኔ አደፍርስ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው በመማሪያ፣ በማደሪያ እና በሌሎች አገልግሎት መስጫ ክፍሎች እና ስፍራዎች ተማሪዎች አካላዊ ርቀታቸውን ጠብቀው እንዲስተናገዱ የሚያስችል ዝግጅት ማድረጉን አስረድተዋል፡፡

ለለይቶ ማቆያ ሲያገለግሉ የነበሩ ክፍሎች፣ መመገቢያ ቤቶች፣ ቤተ መጻሕፍት እና ቤተ ሙከራዎችም የኮሮና ቫይረስ ኬሚካል ርጭት ተደርጎባቸዋል ነው ያሉት፡፡

ውሃን ጨምሮ ለንፅህና መጠበቂያ የሚያገለግል ሳኒታይዘር እንዲሁም የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብሎች አቅርቦትመሟላቱን የገለጹት አቶ ጫኔ፣ ለተማሪዎች አገልግሎት ለሚሰጡ ሰራተኞች ስለ ቫይረሱ ግንዛቤ እንዲኖራቸው መደረጉን አንስተዋል፡፡

ደባርቅ፣ ደብረታቦር እና አርሲ ዩኒቨርሲቲዎችም ትምህርት መጀመር እንደሚችሉም ተገልጿል፡፡

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.