Fana: At a Speed of Life!

ጠ/ሚ ዐቢይ በሸራተን ሆቴል አካባቢ እየተገነባ የሚገኘውን የወንዝ ዳርቻ አረንጓዴ ልማት ፕሮጀክትን ጎበኙ

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 22 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በሸራተን ሆቴል አካባቢ እየተገነባ የሚገኘውን የሸገር የወንዝ ዳርቻ አረንጓዴ ልማት ፕሮጀክትን ጎበኙ፡፡

በጉብኝቱ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማን ጨምሮ ሌሎች የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡

በቻይና መንግስት ድጋፍ የሚከናወነው እና የሸገር ማስዋብ ፕሮጀክት አካል የሆነው ይህ የወንዝ ዳርቻ አረንጓዴ ልማት ፕሮጀክት ግንባታ መስከረም 20 ቀን 2012 ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተገኙበት መጀመሩ የሚታወስ ነው፡፡

በፕሮጀክቱ ከእንጦጦ ተራራ እስከ ባምቢስ ድልድይ ያለው 12 ኪሎ ሜትር ወንዝ እና የወንዝ ዳርቻዎች የሚለማ መሆኑ ታውቋል።

እንዲሁም ከሸራተን ሆቴል ፊት ለፊት ያለው 42 ስኩዌር ኪሎ ሜትር መሬት በፕሮጀክቱ ይለማል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በተጨማሪም በእንጦጦ ተራራ እስከ 100 ሺህ ሰው የሚያስተናግድ የመሮጫ እና የእግር ጉዞ መከወኛ ስፍራ እንደሚገነባም ነው የተነገረው፡፡

በፕሮጀክቱ አምስት ግዙፍ ማዕከላት የሚገነቡ ሲሆን በዚህም መሰረት የስብሰባ፣ የጥበብ ማቅረቢያ ስፍራ፣ የህፃናት መዝናኛ ማዕከል እና የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ማዕከላት እንደሚካተቱበት ተጠቁሟል፡፡

ከተጀመረ ሶስት ወራትን ያስቆጠረው ፕሮጀክቱ 45 በመቶ መጠናቀቁ የተገለፀ ሲሆን በግንቦት ወር እንደሚጠናቀቅ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ በጉብኝቱ ወቅት ገልጸዋል፡፡

በ29 ቢሊየን ብር ወጪ የሚከናወነው የአዲስ አበባ ወንዞች ዳርቻዎች ልማት ፕሮጀክት በሶስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል።

የአዲስ አበባ ወንዞች ዳርቻዎች ልማት ፕሮጀክት አዲስ አበባ ከተማን ለሁለት ከፍለው የሚፈሱ ወንዞች ላይ ያተኮረ ሆኖ ከሰሜን አዲስ አበባ እንጦጦ ተራራ እስከ አቃቂ ወንዝ ያለውን 56 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ነው።

በፕሮጀክቱ በሶስት ዓመታት ውስጥ 4 ሺህ ሄክታር መሬት እንደሚለማ የሚጠበቅ ሲሆን፥ ድልድዮች፣ ሰው ሰራሽ ሐይቆች፣ አረንጓዴ ቦታዎች፣ የመዝናኛ ማዕከላት፣ የውኃ ትራንስፖርት እና የንግድ ማዕከላትን ያካተተ ግንባታ እንደሚካሄድም ታውቋል።

ፕሮጀክቱ የአዲስ አበባ ከተማን የአረንጓዴ ሽፋን ከ0 ነጥብ 3 ወደ 7 በመቶ ከፍ የሚያደርግ መሆኑም ተነግሯል።

በአላዛር ታደለ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.