Fana: At a Speed of Life!

ጠ/ሚ ዐቢይ ኢድ አልፈጥርን ምክንያት በማድረግ ለተለያዩ ወገኖች ስጦታ አበረከቱ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 14 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ኢድ አልፈጥርን ምክንያት በማድረግ ለተለያዩ ወገኖች ስጦታ አበረከቱ።

በቦሌ ክፍለ ከተማ ለሚኖሩ 100 አባ ወራ የሶሪያ ስደተኞች የምግብ፣ የአልባሳት እና የንጽህና መጠበቂያ ስጦታ አበርክተውላቸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ ስጦታውን ባበረከቱበት ወቅት ሶሪያ ኢኮኖሚዋ የዳበረ እና ትልቅ አቅም ያላት እንደነበረች አንስተዋል፡፡

እንዲሁም ዜጎቿ ያን ሃገር ያሳጣቸው ጦርነት እንደሆነም ገልፀዋል፡፡

ሶሪያውያኑም ይህ ጊዜ እስኪያልፍ ኢትዮጵያ ሁለተኛ ሃገራቸው ሆና እንዲኖሩ መንግስት የሚቻለውን ሁሉ ያደርጋል ሲሉም ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ ሁልጊዜም የተቸገሩ ወንድም እና እህቶችን ተቀብላ ለማስተናገድ ዝግጁ መሆኗንም አስታውቀዋል፡፡

ሶራውያኑ በበኩላቸው ዛሬ የተበረከተልን ስጦታ በኢትዮጵያኖች ዘንድ የተሰጣቸውን ትኩረት እና እንክብካቤን እንደሚሳይ ገልፀዋል፡፡

ለዚህም ስለተደረገላቸው ሁሉ ኢትዮጵያን እና ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይን አመስግነዋል፡፡

በሌላ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በክፍለ ከተማው በሁለት ወንድማማቾች እየተረዱ ያሉ 100 ዜጎች ያሉበትን ሁኔታ ጎብኝተዋል።

ዜጎቹ ከዚህ ቀደም በቀን ስራ የሚተዳደሩ የነበሩና በኮቪድ19 ምክንያት ለችግር የተጋለጡ ናቸው።

በጉብኝታቸው ወቅትም የምግብና የእርድ እንስሳት ስጦታ አበርክተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቡል ኸይር የበጎ አድራጎት ድርጅት ተገኝተው ዜጎች እርስ በርስ ለመረዳዳት እያደረጉ ያለውን ጥረት አድንቀዋል።

ለበጎ አድራጎት ድርጅቱም የምግብና የእርድ እንስሳት ስጦታ አበርክተዋል።

ከዚህ ባለፈም በጉለሌ ክፍለ ከተማ በመገኘት ወላጅ አልባ ለሆኑ ህጻናት እና አነስተኛ ገቢ ላላቸው አቅመ ደካማ ወገኖችም የተለያዩ ስጦታዎችን አበርክተውላቸዋል።

በዓላዛር ታደለ

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.