Fana: At a Speed of Life!

ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ ከናይጄሪያው ፕሬዚዳንት መሃሙዱ ቡሃሪ ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 3፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ከናይጄሪያው ፕሬዚዳንት መሃሙዱ ቡሃሪ ጋር ተወያዩ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ፕሬዚዳንት መሃሙዱ ቡሃሪን በዛሬው እለት ነው በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው ያነጋገሩት።

በቆይታቸውም የጋራ ፍላጎት በሚስተዋልባቸው በርካታ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ በዚሁ ወቅት፥ ሀገራዊ አቅምን ከመጠቀም፣ ተለይቶ የታወቀ ብቃት በሚታይባቸው ዘርፎች ምርታማነትን ከማፋጠን እና ብልጽግናን ከመገንባት አኳያ የተከናወኑትን ቁልፍ የሪፎርም ጉዳዮች ገልጸውላቸዋል።

ፕሬዚዳንት ቡሀሪም፥ ኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት ዓመታት ያስመዘገበቻቸውን ለውጦች አስታውሰው፤ ሪፎርሙን በፍጥነት እና በብርቱ አቅም ለማስጓዝ በመቻላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድን አድንቀዋል።

መሪዎቹ ሁለቱ ሀገራት በሚመሳሰሉባቸው እንደ ሕብረ ብሔራዊነት እና የሀይማኖት ብዝሀነት፣ ፌደራሊዝም እና አብላጫውን ቁጥር የሚይዘውን ወጣቱን ኃይል የልማት አንቀሳቃሽ ማድረግ በመሳሰሉ ጉዳዮች ላይ የዕውቀት ልውውጥ ለማድረግ ተስማምተዋል።

በንግድና ኢንቨስትመንት፣ በቱሪዝም፣ በኢነርጂ እና ግብርና ልማት ዘርፎች ትብብር ለማድረግ፣ እንዲሁም ናይጄሪያ በቅርቡ ቁልፍ እርምጃዎችን ባስመዘገበችበት የተመዘበረ ሀብትን ማስመለስ ላይ የልምድ ልውውጥን ለማካሄድ ስምምነት ላይ ደርሰዋል።

በተጨማሪም በሀገራቱ መካከል በሚደረጉ የሁለት የትብብር መስኮች ላይም የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል።

የመግባቢያ ስምምነቱም በመከላከያ ዘርፍ እና የሁለቱን ሀገራት የዲፕሎማቲክ እና የሰርቪስ ፓስፖርት የያዙ ያለ ቪዛ መንቀሳቀስ የሚያስችል ላይ ነው።

የናይጄሪያው ፕሬዚዳንት መሃሙዱ ቡሃሪ 33ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ ላይ ለመካፈል ባሳለፍነው ቅዳሜ ጥር 30 2012 አዲስ አበባ መግባታቸው ይታወሳል።

ፕሬዚዳንት መሃሙዱ ቡሃሪ የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ መጠናቀቅን ተከትሎ በዛሬው እለት በኢትዮጵያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት በማድረግ ላይ ይገኛሉ።

በአላዛር ታደለ

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.