Fana: At a Speed of Life!

ፍርድ ቤቱ የመዛግብት እና የዳኞች ቁጥር አለመመጣጠን ለስራው እንቅፋት እንደሆነበት ገለፀ

አዲስ አበባ፣ ጥር 18 ፣2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የመዛግብት እና የዳኞች ቁጥር አለመጣጣም ለስራው እንቅፋት እንደሆነበት ገለፀ።

ፍርድ ቤቱ በስራ ላይ ያሉ ዳኞች ቁጥር አገልግሎት ለማግኘት ከሚቀርቡ ጉዳዮች ፍሰት ጋር እንደማይጣጣም የስድስት ወር እቅድ አፈጻጸሙን በገመገመበት ወቅት ገልጿል።

ዳኞች ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት መሾማቸው እና በሁለተኛ ዲግሪ መርሃ ግብር የትምህርት እድል እንዲያገኙ መደረጉ እንዲሁም አጠቃላይ የዳኞች ቁጥር ከጉዳዮች ፍሰት አንጻር ዝቅተኛ መሆኑ ችሎቶች በመዝገብ እንዲጨናነቁ ምክንያት ሆኗልም ነው ያለው።

ፍርድ ቤቱ በመንፈቅ ዓመቱ ለ12 ሺህ 667 መዛግብት ዕልባት ለመስጠት ዕቅድ ይዞ ለ9 ሺህ 912 መዛግብት ብቻ ዕልባት መስጠቱንም አስታውቋል።

የሚቀርቡ ጉዳዮች ውስብስብ መሆን፣ በአንድ መዝገብ በርካታ ተከሳሾች መቅረብ እና የምስክር መብዛት ለዕቅዱ አለመሳካት ምክንያት መሆኑንም ጠቅሷል።

በተጨማሪም የችሎት አዳራሽ እጥረት፣ የመቅረጸ ድምጽ አለመሟላት፣ የተቀረጸ ምስክርነት ወደ ጽሁፍ በጊዜው ተገልብጦ አለመቅረብ እና ያልተመቻቸ የስራ ቦታ በዳኝነት ስራው ላይ ተፅዕኖ መፍጠሩም ተነስቷል።

ለችግሩ እልባት ለመስጠትም ፍርድ ቤቱ ያለውን ሃብት በመጠቀም እየሰራ መሆኑን እንዲሁም ተጨማሪ ዳኞች ለማሾም እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ከፍርድ ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.