Fana: At a Speed of Life!

ቋሚ ኮሚቴው የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ተልዕኮውን በአግባቡ እንዲወጣ አሳሰበ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 2፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ብሔራዊ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ተልዕኮውን በአግባቡ ለመወጣት ዝግጁ መሆን ይጠበቅበታል ሲል አሳሰበ፡፡
 
ቋሚ ኮሚቴው ከብሔራዊ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ጋር በኮሚሽኑ የ2015 የበጀት ዓመት ዕቅድ ዙሪያ በዛሬው ዕለት ውይይት አካሂዷል፡፡
 
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ዶክተር ዲማ ነገዎ÷ በሀገራችን በየቦታው በተፈጥሮ እና በሰው- ሠራሽ ችግሮች የተፈናቀሉ የሕብረተሰብ ክፍሎች መኖራቸውን አንስተዋል፡፡
 
ችግሩን ቀድሞ ለመከላከል ኮሚሽኑ የአደጋ ስጋት ተደራሽነትን ማስፋት እንዳለበት ጠቁመው÷ የአደጋ ቅልበሳውን በአግባቡ ለመወጣትም በዕቅድ መንቀሳቀስ እንዳለበት ነው ያሳሰቡት፡፡
 
ቀደም ሲል በተከሰተው የዝናብ እጥረት መንስዔ በድርቅ ተጎጂ ለሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ፈጥኖ ለመድረስ የኮሚሽኑ ቅድመ ዝግጅት አስፈላጊ መሆኑንም በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡
 
ተቋሙ ተልዕኮውን በአግባቡ ለመወጣት በሙያተኛ እና በአደረጃጀት ብቁ ሆኖ መገኘት እንዲሁም ከክልሎች እና ከአጋር ድርጅቶች ጋር ያለው ግንኙነት ግልጽ መሆን እንዳለበት እና የተጠያቂነት አሠራር ሥርዓት ማስፈን እንደሚገባውም እንዲሁ አሳስበዋል፡፡
 
የኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ ዶክተር ፈቲሂ ማህዲ በበኩላቸው÷ የኮሚሽኑ አመራሮች ማብራሪያ እና ምላሽ በሚሹ ጉዳዮች ፈጥነው ምላሽ መስጠት አለባቸው ብለዋል፡፡
 
ለችግር ፈጥኖ መድረስ እና ሙስናን መከላከል የመጪው ዓመት ተቀዳሚ ተግባራቸው ሊሆን እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡
 
የብሔራዊ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ሃይድሩ ሃሰን÷ በኢትዮጵያ ከ15 ነጥብ 4 ሚሊየን በላይ በተፈጥሮ እና በሰው-ሠራሽ አደጋ የተፈናቀሉ የሕብረተሰብ ክፍሎች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡
 
በዝናብ ዕጥረት የሚከሰተውን አደጋ ለመቀልበስም በዕቅድ እየተሠራ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
 
ከቋሚ ኮሚቴው የተነሱ ሀሳቦች ገንቢ እና አስተማሪ በመሆናቸው በግብዓትነት በመጠቀም በዕቅድ አካትተው በትኩረት እንደሚሠሩ ማንሳታቸውን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
 
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
 
 
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.