Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ በተለያየ ጊዜ የተሰረቁ 22 ተሽከርካሪዎች እና 33 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 17፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ፖሊስ በጥናት ላይ ተመስርቶ ባካሄደው ዘመቻ በተለያየ ጊዜ የተሰረቁ 22 ተሽከርካሪዎች እና 33 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታውቋል፡፡
በአዲስ አበባ ፖሊስ ኪሚሽን በወንጀልና ትራፊክ አደጋ ምርመራ ዘርፍ የልዩ ልዩ እና የተደራጁ ወንጀሎች ምርመራ ዳይሬክተር ኮማንደር አለማየሁ አያልቄ÷በመዲናዋ ይስተዋል የነበረውን የተሽከርካሪ ስርቆት ለመከላከል እና ወንጀል ፈፃሚዎችን ህግ ፊት ለማቅረብ ፖሊስ በጥናት ላይ በመመስረት የምርመራ እና የክትትል ቡድን አቋቁሞ ዘመቻ ሲያካሂድ መቆየቱን አንስተዋል፡፡
በተካሄደው ዘመቻም በተለያየ ጊዜ የተሰረቁ 22 ተሽከርካሪዎችን ማስመለሱን መቻሉን ነው የገለጹት፡፡
ተሽከርካሪዎቹ እየተሰረቁ ወደ ሃዋሳ ከተማ እንደሚወሰዱ በምርመራ ማረጋገጥ እንደተቻለ ጠቅሰው÷ ከተሰረቁት ተሽከርካሪዎች መካከል ሰባቱ በአዲስ አበባ መገኘታቸውን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
15 ተሽከርካሪዎች ደግሞ በሀዋሳ ከተማ እና ከሀዋሳ ከተማ 100 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኝ አነስተኛ ከተማ ተይዘው ዛሬ ግንቦት 17 ቀን 2014 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ እንዲመለሱ መደረጉን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
ተሽከርካሪ በመስረቅ፣ የተሰረቀውን ተሽከርካሪ በመግዛት እና በመደለል ተሳትፎ ያደረጉ ከአዲስ አበባ 19 ከሃዋሳ ደግሞ 14 በአጠቃላይ 33 ግለሰቦች ተይዘው ምርመራው እየተካሄደ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
ተሽከርካሪዎቹን ለጥበቃ ምቹ በሆነ ቦታ ባለማቆም በሚፈጠር ክፍተት እና አሽከርካሪዎች የመኪናቸውን ቁልፍ ተሽከርካሪ ላይ ጥለው ሲወርዱ እንዲሁም የተሽከርካሪውን ቁልፍ በልዩ ልዩ አጋጣሚ በማስቀረፅ ወንጀል ፈፃሚዎቹ የስርቆት ወንጀሉን ሲፈፅሙ እንደነበር ተጠቁሟል፡፡
ባለንብረቶችና አሽከርካሪዎች አስፈላጊውን ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባ ያሳሰቡት ኮማንደር አለማየሁ÷ ለዚህ ስራ ስኬታማነት ድጋፍ ላደረጉት የፌዴራል ፖሊስ እና የሲዳማ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ምስጋና አቅርበዋል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.