Fana: At a Speed of Life!

በአይቮሪኮስት ከፕላስቲክ ውጤቶች የመማሪያ ክፍሎች እየተገነቡ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥር 14 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) አይቮሪኮስት በትምህርት ቤቶች የመማሪያ ክፍሎችን ለመገንባት የተጣሉ የፕላስቲክ ውጤቶችን እየተጠቀመች ነው።

በምዕራብ አፍሪካዊቷ ሃገር አይቮሪኮስት ከፍተኛ የመማሪያ ክፍል እጥረት እንዳለ ይነገራል።

በዚህ ሳቢያም 1 ነጥብ 6 ሚሊየን ያህል ህፃናት ወደ ትምህር ቤት እንደማይሄዱ መረጃዎች ያመለክታሉ።

ይህን የመማሪያ ክፍል እጥረት ለመቅረፍም አንድ የኮሎምቢያ ኩባንያ ከተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) ጋር በመተባበር በቆሻሻ መጣያ ስፍራ የተከማቹ የፕላስቲክ ውጤቶችን በመጠቀም የመማሪያ ክፍሎችን መስራት ጀምሯል።

ከፈረንጆቹ 2018 ጀምሮም ከተጣሉ የፕላስቲክ ውጤቶች 26 የመማሪያ ክፍሎች ተሰርተዋል ነው የተባለው።

በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ውስጥም 528 የመማሪያ ክፍሎችን ለመገንባት እቅድ የተያዘ ሲሆን፥ በፕላስቲክ የሚሰሩት መማሪያ ክፍሎች በመደበኛነት ከሚሰሩት ክፍሎች ከወጪ አንጻር በግማሽ ይቀንሳሉም ተብሏል።

የመማሪያ ክፍሎቹ የወዳደቁ የፕላስቲክ ውጤቶችን መልሶ ጥቅም ላይ በማዋል ብቻ የሚሰሩና ምንም አይነት ብሎኬትም ሆነ አሸዋን የማይጠቀሙ ናቸው።

አሁን የተጀመረው ይህ የፈጠራ ስራ ታዲያ በቀጣዮቹ ሁለት አመታት ትምህርትን ለ25 ሺህ ህጻናት ተደራሽ ለማድረግ እንደሚያስችልም ዩኒሴፍ ገልጿል።

በተጨማሪም ዩኒሴፍ በአይቮሪኮስት የፕላስቲክ ጡብ ማምረቻ ፋብሪካ አስገንብቷል።

ፋብሪካው ያለውን የመማሪያ ክፍል እጥረት ከመቅረፉም ባሻገር የተጣሉ የፕላስቲክ ውጤቶችን ለፋብሪካው የሚያቀርቡ ሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ ያለመ መሆኑ ተገልጿል።

አይቮሪኮስት ከምታስወግደው የፕላስቲክ ተረፈ ምርት ውስጥ 5 በመቶውን ብቻ ጥቅም ላይ ማዋሏ ለፕሮጀክቱ መሳካት ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው ታምኖበታል።

ምንጭ፦ ቢቢሲ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.