Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮ-ህንድ የኢንቨስትመንት፣ ንግድ እና ቱሪዝም እድሎች ላይ የቢዝነስ ፎረም ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 21፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮ-ህንድ የኢንቨስትመንት፣ ንግድ እና ቱሪዝም እድሎች ላይ የበይነ መረብ ቢዝነስ ፎረም ተካሄደ፡፡

በህንድ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከዘ-ዲፕሎማቲስት ከተሰኘው የመጽሔት ፕሮዳክሽን ድርጅት ጋር በመተባበር የኢትዮ-ህንድ የኢንቨስትመንት፣ የንግድ እና የቱሪዝም እድሎችን ለማስተዋወቅ ያለመ የበይነ መረብ ቢዝነስ ፎረም አዘጋጅቷል።

በመርሃ ግብሩ በህንድ የኢትዮጵያ አምባሳደር ዶ/ር ትዝታ ሙሉጌታ፣ በኢትዮጵያ የህንድ አምባሳደር ሮበርት ሼትኪንቶንግ እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እንዲሁም ከ45 በላይ የህንድ ኩባንያዎች ተሳትፈዋል።

አምባሳደር ትዝታ ሙሉጌታ በንግግራቸው፥ የህንድ የንግዱ ማህበረሰብ በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋዩን እንዲያፈስ እና ቢዝነስ ለመስራት ያለውን እድልና አቅም ለማስተዋወቅ ፎረሙ ጠቃሚ መሆኑን አመልክተዋል።

አምባሳደር ትዝታ አያይዘውም፥ የኢትዮጵያ መንግስት በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን ማፍሰስ ለሚፈልጉ የውጭ ባለሃብቶች ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር እያደረገ ያለውን ጥረት በዝርዝር አስረድተዋል።

መንግስት ኢትዮጵያን በአፍሪካ ቀዳሚ የማኑፋክቸሪንግ ማዕከል የማድረግ ራዕይ በመያዝ ለኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ከፍተኛ ትኩረት መስጠቱንም አክለው ገልፀዋል ።

በኢትዮጵያ የህንድ አምባሳደር ሮበርት ሼትኪንቶንግ በበኩላቸው፥ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ አስቸጋሪ ወቅት እንኳን ወደ 35 የሚጠጉ የህንድ ኩባንያዎች ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የኢንቨስትመንት ፍቃድ አግኝተዋል ነው ያሉት።

ይህ የሚያሳየውም ኢትዮጵያ ለውጭ ባለሃብቶች ብዙ ያልተነካ እና ግዙፍ የኢንቨስትመንት አቅም እንዳላት ነው ሲሉ አምባሳደሩ አንስተዋል።

ተሳታፊዎች በኢትዮጵያ ያለውን የኢንቨስትመንትና የንግድ እድሎች በተመለከተም ጥያቄዎችን ያነሱ ሲሆን፥ ከአምባሳደሮች እና ጥሪ ከተደረገላቸው እንግዶች ምላሽ እንደተሰጠባቸው ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.