Fana: At a Speed of Life!

በጋምቤላ ክልል በዓመት እስከ 17 ሺህ ቶን የአሳ ምርት ለማምረት የሚያስችል ስምምነት ተደረገ

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 12 ፣2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በጋምቤላ ክልል እስከ 17 ሺህ ቶን የአሳ ምርት ለማምረት የሚያስችል ስምምነት ተፈርሟል ።

በክልሉ የሚገኘውን እምቅ የአሳ ሀብት ልማት ለማሳደግ የሚያስችል ፕሮጀክት ስምምነት በጋምቤላ ክልል፣ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና በጋምቤላ ዩኒቨርስቲ መካከል ተደርጓል።

ፕሮጀክቱ 155 ሚሊየን ብር የሚፈጅ ሲሆን በ3 አመት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሏል።

የጋምቤላ ክልል የአሳ ምርት በአሁኑ ወቅት በአመት እስከ 400 ቶን የሚደርስ ሲሆን ÷ይህ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ ወደ 17 ሺህ ቶን ከፍ ያደርገዋልም ነው የተባለው።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ሲሳይ ቶላ÷ ፕሮጀክቱ በግብርና ምርቶች በቴክኖሎጂ በመደገፍና እሴት በመጨመር በአለም ገበያ ተወዳዳሪ የመሆን ዕቅድ አንዱ አካል ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በውጭ ምንዛሬ ከውጭ የምታስገባውን የአሳ ምርት በማስቀረት የውጭ ምንዛሬ እጥረትን ለመቅረፍም ያስችላል ነው ያሉት።

የጋምቤላ ክልል የብዙ የተፈጥሮ ሀብት ባለቤት ቢሆንም የማምረት ስርዓቱ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ባለመሆኑ ኢትዮጵያ ማግኘት ያለባትን ሀብት ሳታገኝ ቆይታለችም ብለዋል።

የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሙድ ኡጁሉ በበኩላቸው÷ ከዘርፉ ተጠቃሚ ለመሆን ፕሮጀክቱ እስኪጠናቀቅ ድረስ ክልሉ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ የአሳ ምርትን ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ በማቅረብ የሀገሪቱን የአሳ ምርት እጥረትን ያስቀራል ተብሏል።

ፕሮጀክቱ የሀብት እና የስራ እድልን ከመፍጠር በተጨማሪ የአሳ ምርምር ማእከል እንዲሆንም ይጠበቃል ነው የተባለው።

በስምምነቱ መሰረት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የቴክኖሎጂ ፣ ክልሉ የመሬት አቅርቦትን የሚያቀርቡ ሲሆን ÷የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ የምርምር ስራዎችን በመስራት በጋራ እንደሚሰሩ ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል ።

#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.