Fana: At a Speed of Life!

በጋምቤላ ክልል ወደ ስራ ያልገቡ 92 የእርሻ ኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችን ወደ ልማት ለማስገባት እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 13፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በጋምቤላ ክልል 2 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ብድር ተወስዶባቸው ወደ ስራ ያልገቡ 92 የእርሻ ኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችን ወደ ልማት ለማስገባት እየሰራ መሆኑን ገለጸ።
የባንኩ የስራ ኃላፊዎች ከክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ጋር በእርሻ ኢንቨስትመንት ዙሪያ ተወያይተዋል።
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት ዶክተር ዮሃንስ አያሌው እንደገለጹት÷ በክልሉ ከ2 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር በላይ የብድር አገልግሎት ከተሰጣቸው 154 የእርሻ ኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች መካከል በስራ ላይ የሚገኙት 62ቱ ናቸው።
ቀሪዎቹ 92ቱ ፕሮጀክቶች ደግሞ ባለቤቶቹ ልማቱን አቋርጠው መጥፋታቸውን ገልጸዋል፡፡
በዚህም ምክንያት አሁን ላይ በክልሉ ፋይናንስ የተደረጉ ፕሮጀክቶች ወለዱን ጨምሮ 3 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር መድረሱንና መሬቶቹም ከልማት ተስተጓጉለው እንደሚገኙ ጠቁመዋል።
በመሆኑም ባንኩ የእርሻ ኢንቨስትመንቶችን በሃራጅ ሽያጭ ለባለሃብቶች በማስተላለፍ ወደ ልማት እንዲገቡ በትኩረት እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በበኩላቸው፥ ቀደም ሲል በነበሩ ብልሹ አሰራሮች አልሚ ያልሆኑ ባለሃብቶች መሬቱን ለባንክ በማስያዝ የሀገርና ሕዝብን ሀብት ዘርፈው መጥፋታቸውን ተናግረዋል።
የእርሻ ፕሮጀክቶችን ወደ ልማት ለማስገባት በባንኩ የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ እንዲቀጥል መጠየቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.