Fana: At a Speed of Life!

ብልፅግና ፓርቲ ምርጫው በዚህ አመት እንዲካሄድ ጠንካራ አቋም አለው – አቶ ብናልፍ አንዷለም

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 25፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የብልፅግና ፓርቲ የ2012 ብሄራዊ ምርጫ በያዝነው አመት እንዲካሄድ ጠንካራ አቋም መያዙን አስታውቋል።

የፓርቲው የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ትናንት በወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታ እና በሀገራዊ ምርጫው ዙሪያ ተወያይቶ የተለያዩ ውሳኔዎችን ማሳለፉንም ነው የፓርቲው ፅህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ብናልፍ አንዷለም በዛሬው እለት በሰጡት መግለጫ የጠቆሙት።

ብልፅግና ፓርቲ በምርጫው ዙሪያ የአቋም ለውጥ አላደረገም ያሉት ሀላፊው፤ ፓርቲው ምርጫው በዚህ አመት መካሄድ አለበት የሚል እምነት እንዳለው አብራርተዋል።

ይህ ማለት ግን ፈታኝ ነገሮች የሉም ማለት አለመሆኑን ጠቅሰው፥ ስራ አስፈፃሚው በስብሰባው የምርጫው ስጋቶች እና መልካም እድሎች ዙሪያ በስፋት መክሮ የመፍትሄ ውሳኔዎችን ማሳለፉን ነው አቶ ብናልፍ ያነሱት።

ብልፅግና ፓርቲ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆነ ህብረተሰቡ ከምርጫው መካሄድ ጋር ተያይዞ የሚያነሷቸው ስጋቶችን እንደተወያየባቸው የጠቀሱት ሀላፊው፤ የምርጫው መካሄድ አልያም መራዘም የሚያስገኛቸው ጥቅሞች እና ጉዳቶች ላይ በስፋት መምከሩን ተናግረዋል።

“ምርጫው ወቅቱን ጠብቆ የሀገሪቱን የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ እውን ለማድረግ ያግዛል፤ ህብረተሰቡ የመረጥኩት መንግስት ነው የሚያስተዳድረኝ የሚል እምነት እንዲኖረውም ያደርጋል” ነው ያሉት አቶ ብናልፍ በመግለጫቸው።

በብዙ መለኪያዎች ምርጫው ቢካሄድ የተሻለ መሆኑን በስራ አስፈፃሚው ስብሰባ ገምግመናል ያሉት ሃላፊው፤ በሀገሪቱ አሁን ላይ የሚታዩ ችግሮችን ግን በቀላሉ አናያቸውም ብለዋል።

ብልፅግና ፓርቲ የቀደመ አቋሙን ያፀናው ሁሉም የበኩሉን ድርሻ ከተወጣ ችግሮቹን መፍታት እንችላለን ከሚል መነሻ እንጂ ችግር የለም ከሚል አይደለም ሲሉም አብራርተዋል።

የፀጥታ ችግሮቹን ለመፍታት የፀጥታ እና የፍትህ ተቋማት ሀላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል ያሉት ሃላፊው፥ ህብረተሰቡም አጥፊዎችን በማጋለጥ የሰላም ቀናኢነቱን አሁንም አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አውስተዋል።

ተፎካካሪ ፓርቲዎችም አባላት እና ደጋፊዎቻቸውን ሰላምን ከሚያውኩ ተግባራት እንዲያርቁ የበኩላቸውን ሀላፊነት እንዲወጡ ጠይቀዋል።

ህዝቡ የሚወከልባቸው ፓርቲዎች ሀላፊነታቸውን ካልተወጡ ምርጫው ቢራዘምም ችግሩ የመቀጠል እድሉ ሰፊ መሆኑንም አብራርተዋል።

የብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በትናንትናው ስብሰባው የህግ የበላይነትን በማረጋገጥ ሀገሪቱን ወደ ተሟላ መረጋጋት ለመመለስ በየደረጃው ያሉ የፀጥታ መዋቅሮች ፀጥታ የማስከበር ሀላፊነታቸውን በሚገባ እንዲወጡ አቅጣጫ አስቀምጧል።

ስራ አስፈፃሚው በብልፅግና ፓርቲ የ10 አመት እቅድ ላይም ዝርዝር ውይይት አካሂዶ አፅድቆታል።

በፋሲካው ታደሰ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.