Fana: At a Speed of Life!

አሸባሪው ህወሓት የእምነት ተቋማትንና ቅዱሳን መጽሃፍትን በማቃጠል ለሃይማኖቶች ያሳየውን ጥላቻ የሃይማኖት አባቶች አወገዙ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 23፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አሸባሪው የህወሓት ቡድን የእምነት ተቋማትንና ቅዱሳን መጽሃፍትን በማቃጠል ለሃይማኖቶች እያሳየ ያለውን ጥላቻና ንቀት የእስልምና ሃይማኖት አባቶች አወገዙ፡፡

አሸባሪው ህወሓት በወረራ በያዘባቸው አካባቢዎች የእምነት ተቋማትን አውድሟል ፤ አንዳንዶቹን ደግሞ የጦርነት ምሽግ በማድረግ ለሃይማኖትም ሆነ ለሰው ልጆች ክብር የሌለው መሆኑን በተግባር አሳይቷል፡፡

አሸባሪ ቡድኑ ከሰሞኑን በአፋር ክልል ጭፍራና ካሳ ጊታ ግንባሮች በወገን ጦር ሽንፈት ገጥሞት ከመፈርጠጡ በፊት ቅዱስ ቁርዓንን እና መስጂዶችን አቃጥሏል፡፡

ኢዜአ ያነጋገራቸው የእስልምና ሃይማኖት አባቶች እንደሚሉት ÷ አሸባሪ ቡድኑ ህዝበ ሙስሊሙ ከፈጣሪው ጋር የሚገናኝበትን፣ ፈጣሪያውን የሚያመልክበትን ቅዱስ ስፍራ ላይ አረመኔያዊ ተግባር በመፈጸም ሃይማኖቱን የማርከስ ስራ ሰርቷል።

በዚህም ለእስልምና እምነት ያለውን ጥላቻ በተግባር አሳይቷል ነው ያለት፡፡

በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች የኡለማ ምክር ቤት ሥራ አስፈፃሚ እና የሰላምና እርቅ ዘርፍ ኃላፊ ሼህ መሐመድ ሲራጅ ÷ የሽብር ቡድኑ የፈጸመው ተግባር በእስልምና አስተምሮ በእጅጉ የተወገዘ መሆኑን ይናገራሉ፡፡

ህዝበ ሙስሊሙ ድርጊቱን አጥብቆ እንደሚቃወምም ነው የገለጹት፡፡

በእስልምና አስተምህሮ ላይ ምርምር እያደረጉ የሚገኙት ሼክ አህመድ አወል በእስልምና ሃይማኖት ቅዱስ ቁርዓንና መስጂድ ታላቅ ክብር የሚሰጠው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም ቅዱስ ቁርዓንና መስጂድን በማቃጠል በዓለም ላይ ላሉ የእስልምና እምነት ተከታዮች ያለውን ጥላቻ በግልጽ ማሳየቱን ነው የገለጹት፡፡

ሼህ መሐመድ ሲራጅ እንዳሉትም ÷ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ይህንን ተግባር እንቃወመዋለን ፤ እናወግዘዋለንም ያሉ ሲሆን ÷ እንዲህ አይነቱን የረከሰ እና የጎደፈ ነገር በመተባበር ከላያችን ላይ መጥረግ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ሼክ አህመድ አወል በበኩላቸው ÷ “መስጂዶችን መንካት ማለት የሰው ልጅ መብት መንካት ማለት ነው ፤ መስጂዶችን ማፍረስ የሰው ልጆች መብት ማፍረስ ነው ፤ የሰው ልጅ ከሃይማኖት ቦታዎች ጋር ያለው ትስስር ብርቱ ነው ብለዋል፡፡

እንደአጠቃለይ ተግባሩ ከማህበረሰብ እና ህዝበ ሙስሊሙ ጋር መጣላት እንደሆነ አክለው ገልጸዋል።

አሸባሪው ቡድን ቅዱስ ቁርዓንና መስጂዶችን ከማቃጠል ባሻገር በእምነት ቦታዎች ላይ ወንጀል መፈጸሙንም ነው ያነሱት፡፡

በዚህም “ባለቤቱን ካልናቁ አጥሩን አይነቀንቁ” እንዲሉ ለእምነትና ለእምነቱ ተከታዮች ያለውን ንቀትና ጥላቻ ማሳየቱንም ነው ያብራሩት፡፡

ሼህ መሐመድ ሲራጅ እንደገለጹት ÷ መስጂድ ተቃጥሏል ፤ ቁራን ተቃጥሏል ወንጀልም ተሰርቷልም ነው ያሉት፡፡ ሼክ አህመድ አወል- በዓለም አቀፍ የጦርነት ህጎች መርሆች መነካት የሌለባቸው ነገሮች አሉ ያሉ ሲሆን ÷ ሃይማኖት ቦታዎችን መንካት ማህበረሰብ መናቅና የማህበረሰብ ማንነትን መንካት ተደርጎ የሚቆጠር ተግባር እንደሆነ አመልክተዋል፡፡

አሸባሪው ህወሓት ሰሞኑን በአፋር ክልል ካቃጠለው ቅዱስ ቁርዓን ላይ “የጀሃነብ እሳት መቀጣጠያ ናቸው” የሚለው ቃል እንደተረፈ ገልጸው ÷ ይህም የሽብር ቡድኑ አባላት ከፈጣሪ ቁጣ እንደማይተርፉ አመላካች መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አሸባሪ ቡድኑ በየትኛውም የእምነት ተቋማት ላይ እያደረሰ ያለውን ውድመት እንደሚያወግዙ የገለጹት የሃይማኖት አባቶቹ ÷ በመሆኑም የሽብር ቡድኑን በተባበረ ክንድ መመከት አለብን ብለዋል፡፡

በአሸባሪ ቡድኑ በወረራ ከቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን በመደገፍ ረገድ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የበኩሉን ሚና እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.