Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ እና ህንድ በማህበራዊ ጉዳዮች ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር ተስማሙ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 3፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳዮች ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ከህንድ የማህበራዊ ፍትሕ እና ማብቃት ሚኒስትር ዶክተር ቬሬንድራ ኩማር ጋር በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የማህበራዊ ግንኙነት ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ በኒውደልሂ ተወያይተዋል።

በውይይታቸውም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ስትራቴጂክ ወደ ሆነ አጋርነት ማሳደግ እንደሚያስፈልግ ባለስልጣናቱ ተስማምተዋል።

በአቅም ግንባታ ፕሮግራሞች፣ በስራ እድል ፈጠራ፣ የወጣቶች ስልጠና እንዲሁም የኢኮኖሚ ችግር ያለባቸው የህብረተሰብ ክፍሎችን ማገዝ በሚቻልበት ጉዳይ ላይም ተወያይተዋል።

በተለይ አካል ጉዳተኞችን ማብቃት፣ የእፅ ተጠቃሚነትን መከላከል እና መልሶ ማቋቋም እንዲሁም አረጋውያንን በተመለከቱ በልዩ ሁኔታ ለመስራት ተስማምተዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት የአረጋውያን ማዕከል ለማቋቋም አዲስ ፕሮጀክት ቀርፆ እየሰራ እንደሚገኝ ዶክተር ኤርጎጌ የገለፁ ሲሆን÷ ማዕከሉን ለማቋቋም ከህንድ ትልቅ ልምድ እንደሚወሰድ ተናግረዋል።

የህንድ መንግስት በኢትዮጵያ የትምህርት ስርዓት ውስጥ የሚያደርገውን ድጋፍ አድንቀው ለኢትዮጵያውያን ተማሪዎች በተለያዩ ጊዜያት የሚሰጠውን የትምህርት እድል አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

የህንዱ የማህበራዊ ፍትህ እና ማብቃት ሚኒስትር ዶክተር ቪሬንድራ ኩማር በበኩላቸው÷ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ሁሉን አቀፍ ግንኙነት የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል።

ሀገራቸው ይህን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ፍላጎት እንዳላት ተናግረዋል።

በተለይም የኢትዮጵያ መንግስት የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ ያደረገው ጥረት መንግስት ለጾታ እኩልነት ለሰጠው ትኩረት ማሳያ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.