Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ ያጋጠሟትን ችግሮች ለመፍታት በህብረት መቆም እንደሚገባ ፖለቲከኞች ገለፁ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 20፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢትዮጵያ አሁን የገጠሟትን ችግሮች ለመፍታት እንደ አድዋው ድል በህብረት መቆም እንደሚገባ ፖለቲከኞች ገለፁ።

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የአድዋ ድል በዓልን አስመልክቶ ያነጋገራቸው ፖለቲከኞች በጋራ እውነተኛ ዴሞክራሲ ስርአትን ለመገንባት መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።

የአድዋ ድልን ለሀገራዊ መግባባት መጠቀም እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።

ቀድሞ የነበረው የኢትዮጵያውያን ህብረት እና አንድነት አሁን ካጠላው የመገፋፋት ፖለቲካ አንጻር የአድዋ ድልን የማይመጥን እና በድሉ ክብር ልክ ያልተጠቀምንበት ነው ሲሉም ያነሳሉ።

ከዚህ ባለፈ ግን የአድዋ ድል ትቶት ያለፈውን እሴት በተጨባጭ ትውልዱ እንዳልተጠቀመበትም አስረድተዋል።

ሃገር ፈተና ውስጥ በገባች ጊዜ ህዝቦች በትብብር ቆመዋል የሚሉት ፖለቲከኞቹ፥ ዘንድሮም የህዝቦች አንድነት ሀገሪቱ ለገጠማት ችግር መሹለኪያ ሊሆን ይገባል ብለዋል።

ወራሪን ያሳፈረው የአባቶች ታሪክ ዛሬ ላይ ካለው የጥላቻ እና የልዩነት ታሪክ ወጥቶ ለሀገር ሰላም በሚጠቅም መልኩ ሊሰራበት እንደሚገባም አንስተዋል።

በጋራ ዴሞክራሲያዊ ስርአት መፍጠር የአሁኑ ትውልድ ሀላፊነት በመሆኑ፥ ሀገርን እና ከአባቶች የተሻገረውን የህብረት አሻራ ጠብቆ ለማቆየት ማስተዋል እንደሚገባም አንስተዋል።

የአድዋ ድል ዝክር በተለይም ወጣቱ ሀገራዊ ፍቅር እና ተቆርቋሪነት ውስጥ እንዲገባ ሊነገርና በአግባቡ ጥቅም ላይ መዋል የሚገባው እንደሆነም ገልጸዋል።

አሁን እውነተኛ ዴሞክራሲን ለመገንባት የምንሰራበት ወቅት እንደመሆኑ ከአባቶች የቀደመ ታሪክ ልንማር ይገባልም ነው የሚሉት አስተያየት ሰጭዎቹ።

አያይዘውም በፖለቲካ ውስጥ ያሉ አካላት የራስን ሀቅ ሸሽቶ ህዝቦችን ለመነጣጠል ትርክትን ከመስበክ ሊቆጠቡ እንደሚገባም አውስተዋል።

በሃይለእየሱስ መኮንን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.