Fana: At a Speed of Life!

ከግለሰብ እስከ ሃገር ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ የሚገኘውን ህገወጥ የጦር መሳሪያ ሽያጭና ዝውውርን ለመከላከል ተባብረን ልንቆም ይገባል – ወይዘሮ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 17፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በዓለም ላይ ከግለሰብ እስከ ሃገር ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ የሚገኘውን ህገወጥ የጦር መሳሪያ ሽያጭና ዝውውርን መከላከል እንደሚገባ የኢፌዴሪ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ አሳሰቡ።

ጠቅላይ አቃቤ ህጓ ኢትዮጵያን ህገወጥ የጦር መሳሪያ ሽያጭና ዝውውር ከሚያመጣው ችግር ለመታደግ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፀደቀው የጦር መሳሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ መውጣቱን አስመልክተው መልዕክት አስተላልፈዋል።

በፈስቡክ ገፃቸው ባስተላለፉት መልዕክት አሁን ላይ ህገወጥ የጦር መሳሪያ ሽያጭና ዝውውር የመላው አለም ፈተና መሆኑን አንስተዋል።

ይህን ከግለሰብ ጀምሮ እስከ ቤተሰብ፣ ማህበረሰብ እና ሃገር ድረስ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ የሚገኝን ወንጀል ሁሉም ሰው ለመከላከል ተባብሮ እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል።

የጦር መሳሪያ ቁጥጥር የሀገርንና የህዝብን ሰላምና ፀጥታ ለማስጠበቅ እንዲሁም የዜጎችን እና የህዝቦችን መብትና ደህንነት ለማስከበር አስፈላጊ መሆኑን በመገንዘብ የተዘጋጀ ነው።

እንዲሁም ግለሰቦች የታጠቋቸውን የጦር መሳሪያዎች የህብረተሰቡን ሰላምና ፀጥታ ለማስጠበቅ ተግባር ሊውሉ የሚችሉበትን እድል መፍጠር አስፈላጊ በመሆኑም ነው።

አዋጁ ከፍቃድ ውጪ የጦር መሳሪያ፣ የጉዳት ማድረሻ እቃ፣ የጦር ሜዳ መነጽር፣ በጦር መሳሪያ ላይ ሊገጠም የሚችል ማንኛውም አይነት መነጽር ወደ ሀገር ማስገባት፣ ከሀገር ማውጣት፣ መያዝ፣ ማስቀመጥ፣ ማከማቸት፣ መገልገል፣ ማሳየት፣ መደለል፣ መሸጥ፣ መግዛት፣ ማስተላለፍ፣ ማዘዋወር፣ ማጓጓዝ፣ ማምረት፣ ማሰልጠንና ማስወገድን ይከለክላል።

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.