Fana: At a Speed of Life!

ኮሚሽኑ በሚቀጥሉት 10 አመታት የልማት አካታችነትን በማረጋገጥ ፍትሃዊ እድገትን ለማረገጥ እንደሚሰራ አስታወቀ

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 22 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በሚቀጥሉት 10 አመታት የልማት አካታችነትን በማረጋገጥ ፍትሃዊ እድገትን ለማረገጥ እንደሚሰራ የፕላንና ልማት ኮሚሽን አስታወቀ።

ኮሚሽኑ በ10 ዓመቱ መሪ እቅድ ዙሪያ ከፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጋር ውይይት እያካሄደ ይገኛል።

ኮሚሽነር ዶክተር ፍጹም አስፋው እንዳስታወቁት ባለፉት አመታት እድገት ሲመዘገብ ቢቆይም የአስተማማኝነት ችግር ያለበትና ከድህነት ለመላቀቅ በቂ አልነበረም ብለዋል።

በተለይ ባለፉት አመታት የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባት፣ የዋጋ ንረት፣ ከፍተኛ የስራ አጥነት ቁጥር፣ የእዳ ጫና፣ ለተጽእኖ ተጋላጭ የሆነ ኢኮኖሚ፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ የመሰረተ ልማት ጥራት መጓደል እንዲሁም የጤና እና ትምህርት ጥራት መጓደል ችግሮች እንደነበሩም ተጠቅሷል።

ይህንን ችግር ለመቅረፍ ያስችላል የተባለለት የ10 ዓመት እቅዱ ዘጠኝ የትኩረት መስኮችን ለይቷል።

ከእነዚህ መካከል የፋይናንስ ዘርፍ ልማት፣ የብዝሃ ዘርፍ የኢኮኖሚ እድገት ምንጮች፣ የመሰረተ ልማት ዘርፍ፣ የከተማ ልማት ዘርፍ እንዲሁም የሰላምና ደህንነት ዘርፍ ይገኙበታል።

የልማት እቅዱ 10 ምሰሶዎችን የያዘ መሆኑም የፕላን እና ልማት ኮሚሽነሯ ዶክተር ፍጹም አብራርተዋል።

በዚህም በ2022 ዓ.ም የ10 ነጥብ 2 በመቶ ምጣኔ ሃብታዊ እድገት ለማስመዝገብ ታቅዷልም ነው ያሉት።

በሌላ በኩል ከ10 ዓመት በኋላ የሚኖረውን የዜጎችን የነብስ ወከፍ ገቢ አሁን ካለበት 1 ሺህ 70 የአሜሪካ ዶላር ወደ 2 ሺህ 247 የአሜሪካ ዶላር ለማሳደግ መታቀዱንም አስረድተዋል።

ከዚህ ባለፈም ድህነትን ከ19 በመቶ ወደ 7 በመቶ ለመቀነስ ታቅዷልም ነው ያሉት ኮሚሽነሯ።

ግብርናው ከጠቅላላ የሃገር ውስጥ ምርት እድገት አሁን ካለው ድርሻ የመቀነስ ነገር ግን ምርትና ምርታማነትን የማሳደግ እንዲሁም የኢንዱስትሪ እና የአገልግሎት ዘርፎችን በተገቢው ጥራት ለማሳደግ መታቀዱንም አውስተዋል።

ለዚህም በሃገሪቱ ያለውን እምቅ አቅም የመለየት ስራ ይሰራል ተብሏል።

የትኛውም የመንግሥት ስርዓት ቢመጣ ነገሮችን እንደ አዲስ የሚጀመር ሳይሆን እቅዶቹን ተቀብሎ እንዲያስተገብራቸው ለማስቻል ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ያማካለ ውይይቶችን ማድረግ ማስፈለጉ ተገልጿል።

በምስክር ስናፍቅ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.