Fana: At a Speed of Life!

ውጤት ላስመዘገቡ አትሌት እና አሰልጣኞች ሽልማት ተበረከተ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 6፣ 2012 ኤፍ.ቢ.ሲ) በአህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ ውጤት ያስመዘገቡ አትሌቶች እና ባለሙያዎች የማበረታቻ ሽልማት ተበረከተላቸው።

የእውቅናና የማበረታቻ ሽልማቱ በ17ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና፣ በ12ኛው መላ አፍሪካ ጨዋታዎች፣ በ6ኛው የአፍሪካ ኢንተርናሽናል ቴኳንዶ ሻምፒዮን፣ በ1ኛው የአፍሪካ መስማት የተሳናቸው አትሌቲክስ ሻምፒዮና እና በምስራቅ አፍሪካ ጠረጴዛ ቴኒስ ተወዳድረው ውጤት ላስመዘገቡ አትሌቶች፣ አሰልጣኞችና የልዑካን ቡድኑ አባላት የተበረከተ ነው።

በካፒታል ሆቴል በተደረገው የእውቅናና የማበረታቻ ሽልማት መንግስት 5 ሚሊየን ብር ወጪ ማድረጉን ከስፖርት ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በዚህ መሰረት በዓለም ሻምፒዮና ወርቅ ላመጡ 80 ሺህ፣ ብር ላመጡ 60 ሺህ እንዲሁም ነሃስ ላመጡ 40 ሺህ ብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

ለአሰልጣኞች ደግሞ 60 ሺህ፣ 50 ሺህ እና 40 ሺህ ብር እንደ ቅደም ተከተላቸው ተሸልመዋል።

በመላ አፍሪካ ጨዋታዎች ደግሞ ወርቅ ላመጡ 40 ሺህ፣ ብር ላመጡ 30 ሺህ እንዲሁም ነሃስ ላመጡ 20 ሺህ፤ ለአሰልጣኞች ደግሞ 30 ሺህ፣ 25 ሺህ እና 20 ሺህ ብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

ኢትዮጵያ በ17ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና 2 ወርቅ፣ 6 ብር እና 1 ነሃስ፣ በ12ኛው መላ አፍሪካ ጨዋታዎች 6 የወርቅ፣ 5 የብር እና 12 የነሃስ፣ በአፍሪካ ኢንተርናሽናል ቴኳንዶ ሻምፒዮና 5 ወርቅ፣ 2 ብር እና 2 ነሃስ፣ በ1ኛው መስማት የተሳናቸው ሻምፒዮና 2 ወርቅ፣ 3 ብር እና 2 ነሃስ እንዲሁም በምስራቅ አፍሪካ ጠረጴዛ ቴኒስ ውድድር 1 ወርቅ እና 2 ነሃስ ሜዳሊያ ማስመዝገቧ ይታወሳል።

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.