Fana: At a Speed of Life!

የአማራ ባለሃብቶች በአሸባሪው ትህነግ ቤታቸው ለፈረሰባቸው ወገኖች ድጋፍ አደረጉ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 15፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ)የአማራ ባለሃብቶች 4 ሚሊየን ብር ወጪ የተደረገበት 10 ሺህ የቤት ክዳን ቆርቆሮ በሰሜን ጎንደር ዞን በአሸባሪው የትህነግ ቡድን ቤታቸው ለፈረሰባቸው ወገኖች ድጋፍ አድርገዋል፡፡
በወቅቱ በማኅበረሰቡ ላይ የደረሰው ጉዳት ተጠንቶ ከተነገራቸው አስፈላጊ የሆነውን ሁሉ ለማገዝ ቃል በገቡት መሠረትም÷ ቤት ለፈረሰባቸው የሰሜን ጎንደር ዞን ወገኖች የቤት ክዳን ቆርቆሮ ድጋፍ እንዳደረጉ ተገልጿል፡፡
በድጋፍ ርክክቡ የባለሀሃብቶቹ ተወካይ አቶ ዮናስ መኮንን አሸባሪው ቡድን ጦርነት በከፈተባቸው አካባቢዎች ለችግር የተጋለጡ ወገኖች ሁኔታ እንደሚያሳስባቸው ነገልጸዋል፡፡
ለችግር የተዳረጉ ወገኖች ከገንዘብ ጀምሮ ያጡትን ንብረት ሁሉ በማሟላት በቋሚነት ለማቋቋም መታሰቡንም ነው የተናገሩት፡፡
ተጎጂ ወገኖች ኢትዮጵያውያን ከጎናቸው እንደሆኑ እና አስፈላጊ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ማሰብ አለባቸው ብለዋል፡፡
ባለሀብቶቹ በዳባት ወረዳ ጭና ቀበሌ ተገኝተው በአሸባሪው ቡድን ቤታቸው ሙሉ በሙሉ ለወደመባቸው ሁለት አርሶ አደሮች ለእያንዳንዳቸው 40 የቤት ክዳን ቆርቆሮ አበርክተዋል፡፡
በዕለቱ 40 ቆርቆሮ የተበረከተላቸው ወይዘሮ ዓለሚቱ ዘለቀ ‟በጭና ቀበሌ አሸባሪው ቡድን በከፈተው ጦርነት በፈጣሪ ፍቃድ ከሞት ብንተርፍም ቤታችን ሙሉ በሙሉ ወድሟል፤ ንብረታችንም ተዘርፏል“ብለዋል፡፡
ሕዝቡ በሚያደርግላቸው ድጋፍ ሐዘናቸውን ረስተው መጽናናት እንደቻሉም ገልጸዋል፡፡
ሌላኛው 40 ቆርቆሮ የተበረከተላቸው አቶ ሰጠኝ ደሳለኝ አሸባሪው ቡድን መኖሪያ ቤቶችን ምሽግ አድርጎ እንደነበር ነግረውናል፡፡
የእህል ጎተራ ሳይቀር ሰው ይኖርበታል በሚል ያፈርሱት እንደነበር የገለጹት አቶ ሰጠኝ÷ ‟የሰውን ልጅ ቀርቶ ውሻና ድመት ሳይቀር ገድለዋል” ብለዋል፡፡
አሸባሪው እና ወራሪው ቡድን ቢጎዳቸውም ወገናቸው ከምግብ ጀምሮ እስከ አልባሳት እንደደገፋቸው አንስተዋል፡፡
በድጋፍ ርክክቡ የሰሜን ጎንደር ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሠላምይሁን ሙላት ባለሀብቶች ከዚህ በፊት በተፈናቃይ ወገኖች ላይ ያለውን ችግር በአካል ተገኝተው በማየት 800 ኩንታል ፍርኖ ዱቄት ድጋፍ ማድረጋቸውን አስታውሰዋል፡፡
ዛሬም በአሸባሪው ቡድን ቤት የፈረሰባቸውን ወገኖች ተመልክተው 10 ሺህ የቤት ክዳን ቆርቆሮ በተወካዮቻቸው አማካኝነት ድጋፍ ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡
በዞኑ በአሸባሪው የትህነግ ቡድን የተፈናቀሉ ወገኖችን ከማህበረሰቡ ጋር በመቀናጀት እና ኢትዮጵያውያን በሚያደርጉት ድጋፍ እንዳይራቡ ለማድረግ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
ጦርነቱ በድል እስከሚጠናቀቅ ድረስ እና ከተጠናቀቀ በኋላም በተጠና መንገድ በአሸባሪው የትህነግ ቡድን ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የሥነ ልቦና ምክር አገልግሎትን ጨምሮ ቋሚ ድጋፎችን የማድረግ ሥራ እንደሚሠራም አቶ ሠላምይሁን መጠቆማቸውን የዘገበው አሚኮ ነው፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.