Fana: At a Speed of Life!

የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት 8ኛ አመት የስራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ነው

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 25 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት 8ኛ አመት የስራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ጉባኤውን ማካሄድ ጀመረ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ የከተማ አስተዳደሩን የ2013 ዓ.ም የስድስት ወራት የስራ አፈፃፀም ሪፖርት ለምክር ቤቱ አቅርበዋል፡፡

በዚህ ወቅትም የከተማዋን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ የከተማው የጸጥታ ሃይል ከምንጊዜውም በላይ ህዝብን በማሳተፍ የሰራው ስራ የሚያስመሰግን መሆኑን አንስተዋል።

የሰላም ምክር ቤት በማቋቋም ህዝቡን በማሳተፍና የጸጥታ ምክር ቤት ተደራጅቶ ቅንጅታዊ ስራ እንዲኖር ላቅ ያለ አስተዋጽኦ መደረጉንም ተናግረዋል።

የጁንታውን የጥፋት ተልዕኮ ለማክሸፍና ሰላምን ለማስጠበቅ በተሰራው ስራ የተለያዩ የጦር መሳሪያዎች በህብረተሰቡ ጥቆማ መያዙን አስታውሰዋል።

ከዚህ ባለፈም ሰላም ለማደፍረስ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር በማዋል የምርመራ መዝገብ እንዲከፈት መደረጉን ጠቅሰዋል።
የከተማዋን እድገት በሚመጥን ደረጃ የጸጥታ ተቋማትን ከማጠናከር አንጻር 2 ሺህ 674 የሚሆኑ የደንብ ማስከበር አባላትና 4 ሺህ 300 ምልምል ፖሊሶችን መሰልጠናቸውንም አስረድተዋል፡፡

ፖሊስ ጣቢያ ባልነበራቸው 60 ወረዳዎች ፖሊስ ጣቢያ እንዲኖራቸው የማድረግ ስራ መሰራ መሰራቱን በመጥቀስም፥ 189 የእሳት አደጋ ባለሙያዎች ሰልጥነውና ተመርቀው ወደስራ መሰማራታቸውንም አውስተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈጉባኤ ወይዘሮ ዘርፈሽዋል ንጉሴ በበኩላቸው በበጀት ዓመቱ 6 ወራት በከተማዋ በማህበራዊ ፣ኢኮኖሚያዊ እና ሌሎች ዘርፎች አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል ።

በተለይ የተጀመሩ ልዩ ልዩ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለህዝብ አገልግልት እንዲውሉ መደረጉ፣ ለረጅም አመታት ሲንከባለሉ የመጡ ህገወጥ የመሬት ወረራ እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የተወሰደው ህግን የማስከበር እርምጃ ፣ለመከላከያ ሰራዊት የተደረገው ድጋፍ ፣ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ድጋፍ ፣ የተማሪዎች ምገባ፣ የላፍቶ እና ሌሎች የገበያ ማዕከላት እና የአበበች ጎበና የእናቶች እና ህጻናት ሆስፒታል ተጠናቀው ለአገልግሎት መዋል፣ የአዳዲስ ሆስፒታሎች እና ሌሎችም ፕሮጀክቶች እንዲጀመሩ የተደረገውን ስራ ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡

በቀሪ ስድስት ወራትም የተጀመሩ ስራዎች ይበልጥ ተጠናክረው እንዲቀጥል እና 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ በትኩረት መሰራት አለበት ብለዋል፡፡

በ8ኛ አመት የስራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ጉባኤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የ2013 ዓ.ም የስድስት ወራት የስራ አፈፃፀም ሪፖርት ላይ ሰፊ ውይይት እንደሚደረግ ይጠበቃል፡፡

በተጨማሪም የከተማ አስተዳደሩ ፍርድ ቤቶች የ2013 ዓ.ም የስድስት ወራት የስራ አፈፃፀም ሪፖርት የሚገመገም ሲሆን ልዩ ልዩ ሹመቶችንም ያጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል ፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.