Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያን አንድነት በማናጋት ሀገሪቱን ለመበታተን የሚንቀሳቀሱ የጥፋት ሃይሎችን ለመመከት ዘብ እንቆማለን-የምርምር ዩኒቨርሲቲዎች

አዲስ አበባ፣ ሃምሌ 27፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያን አንድነት፣ ሰላምና ብልጽግናን በማናጋት ሀገሪቱን ለመበታተን እና ኢትዮጵያዊ ማንነታችንን ለማጥፋት ከውጪም ሆነ ከውስጥ የሚንቀሳቀስን የጥፋት ሀይሎች በእዉቀታችን ፣ በገንዘባችን፣ በደማችን እና በአጥንታችን እንመክታለን አሉ የምርምር ዩኒቨርሲቲዎች፡፡
 
የምርምር ዩኒቨርስቲዎች የእቅድ ግምገማ በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ የአቋም መግለጫ በማውጣትና ችግኝ በመትከል ተጠናቋል፡፡
በቢሾፍቱ ከተማ ለተከታታይ ሁለት ቀናት ሲካሄድ የነበረዉ የምርምር ዩኒቨርስቲዎች የ2013ዓ.ም የእቅድ አፈጻጸም እና የ2014ዓ.ም እቅድ ስልጠናዊ ግምገማ በዛሬ ከሰዓት ውሎዉ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንሰሳት ጤና ምርምር ኮሌጅ እና አዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲዎች ተጎብኝተዋል፡፡
 
በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የችግኝ ተከላ እና የልህቀት ማዕከል ግንባታ ጉብኝት የተካሄደ ሲሆን÷ በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ ባለ ሰባት ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ተጠናቋል፡፡
 
የአቋም መግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ይቀርባል፡-
 
1) በአገር አቀፍ ደረጃ ለምርምር እና ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲዎች የተሰጡ ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎችን በላቀ ደረጃ ለማሳካት ቃል እንገባለን!
 
2) የአገራችንን የህዝቦች አንድነት፣ ሰላምና ብልጽግናን በማናጋት ኢትዮጵያን ለመበታተን እና ኢትዮጵያዊ ማንነታችንን ለማጥፋት ከዉጪም ሆነ ከዉስጥ የሚንቀሳቀስን የጥፋት ሀይሎች በእዉቀታችን ፣ በገንዘባችን፣ በደማችን እና በአጥንታችን በመመከት አገራችንን ለመታደግ ዘብ እንቆማለን!
 
3) እኛ የምርምር እና የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲዎች ከአባቶቻችን የተረከብናትን ኢትዮጵያን ጥቃትዋን ተከላክለን ሰላማዊና የለማች ሀገር ለልጆቻችን ለማስረከብ የሚጠበቅብንን ድርሻ ለመወጣት ቃል እንገባለን!
 
4) ለህግ እንቆማለን የሚሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት አሸባሪዉ ቡድን እየፈጸመ ያለዉን ጥፋት በመረዳት ከኢትዮጵያ መንግስት ጎን በመቆም እና በአለም አቀፍ ህግ ጭምር እንዲጠየቅ ሊሰሩ ይገባል!
 
5) በአለም አቀፍ ህግ ወንጀል የሆነዉን ህጻናትን ለዉትድርና መመልመል አጥብቀን እንቃወማለን ! ህጻናት ትምህርት እንጂ ሞት አይገባቸዉም! አሸባሪው በህግ እንዲጠየቅ አበክረን እንጠይቃለን!
 
6) አባይ ከኢትዮጵያ ማህጸን የሚመነጭ ዉድ ልጇ፣ የህዳሴዉ ግድብም ለዘመናት ከተፈታተነን ድህነት ለመላቀቅ በራሳችን የጀመርነዉ የህልዉናችን መገለጫ ነዉና ፍትሀዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ምሁራዊ ሚናችንን እንወጣለን!
 
7) በአገር አቀፍ ደረጃ እየተተገበረ ያለዉን የአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራም በማስቀጠል ኢትዮጵያን አረንጓዴ የማልበስ ድርሻችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ማለታቸውን ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
 
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.