Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያን የኤሌክትሪክ ኃይል ዘርፍ ሪፎርም ፍኖተ ካርታ የተመለከተ ውይይት እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፣ መስከረም 20፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያን የኤሌክትሪክ ኃይል ዘርፍ ሪፎርም ፍኖተ ካርታ የተመለከተ ውይይት ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተካሄደ ነው።
በውይይቱ ላይ የገንዘብ ሚኒስቴርን ጨምሮ ሌሎች የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ተሳታፊዎች ናቸው፡፡

የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ስለሺ በቀለ የኤሌክትሪክ ዘርፉ ሪፎርም ፍኖተ ካርታ በውሀ መሥኖና ኢነርጂ ፤ በገንዘብ ሚኒስቴር እንዲሁም በዓለም ባንክ መከናወኑን ገልጸዋል።

የሪፎርም ፍኖተ ካርታው ዋና አላማ የኤሌክትሪክ ፍኖተ ካርታ ዘርፉ ያለበትን ችግር በመፍታት የውጭ ምንዛሬ ማምጣት መሆኑንም አስረድተዋል።

ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ ሊለማ የሚችል ከፍተኛ የታዳሽ ሃይል መኖሩን አስታውሰው ሪፎርሙ ይህንን ሀይል ተጠቅሞ የኢትዮጵያን ህዝብ ሙሉ በሙሉ የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ያደርጋልም ብለዋል።

የግል ባለሀብቱን በአዲስ ኃይል ማመንጫ ከማሳተፍ በተጨማሪ እየተከናወኑ ባሉ የኃይል ማመንጫ ሥራዎች ላይ ማሳተፍ ይገባልም ነው ያሉት።

ከአንድ ዓመት በፊት በተከናወነው የኤሌክትሪክ ዘርፍ ሪፎርም የእዳ ማቃለያ እና የታሪፍ ማስተካከያ ጥናትን ጨምሮ አምስት ዋና ዋና የዘርፉ ማሻሻያ ስራዎችን ያካተተ መሆኑን ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

ይህ የኤሌክትሪክ ፍኖተ ካርታ በዘርፉ የወደፊት እድገት ላይ አስተዋጽኦው ከፍተኛ መሆኑን የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.