Fana: At a Speed of Life!

የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ኮቪድ19ኝን ለመከላከል ለሚደረገው ጥረት ወደ 51 ሚሊየን ብር የሚጠጋ ድጋፍ አደረገ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 28 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት የኮቪድ19ኝን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ ወደ 51 ሚሊየን ብር የሚጠጋ የገንዘብ ድጋፍ አደረገ።

ድጋፉ ከሰራዊቱ የሁለት ወር ደመወዝ ተቀንሶ የሚሰጥ ነው ተብሏል።

የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጀኔራል አደም መሃመድ፥ ድጋፉ ሰራዊቱ ሃገር ከመጠበቅ በተጓዳኝ ህዝባዊነቱን ለማሳየት ያደረገው መሆኑን ገልጸዋል።

ሰራዊቱ የሚያደርገውን ድጋፍ በቀጣይም አጠናክሮ ይቀጥላልም ነው ያሉት።

የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ሰራዊቱ በተለያዩ መንገዶች የሃገር ህልውና እንዲቀጥል የሚያደርገው ጥረት የሚደነቅ ነው ብለዋል።

በተለይም ሃገሪቱ ውጥረት ውስጥ በምትገባበት ጊዜ በዚህ ደረጃ ህዝባዊነቱን ማሳየቱ የሚጠበቅ መሆኑን አንስተዋል።

የኮቪድ19 ወረርሽኝ መከላከልና መቆጣጠር የሚኒስትሮች ኮሚቴ አስተባባሪ ሴክሬታሪያትና የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚል በበኩላቸው፥የተደረገውን ድጋፍ አድንቀው ድጋፉ ወደ 2ኛው የድጋፍ አሰባሰብ መርሃ ግብር እየተገባ ባለበት ወቅት የተደረገ በመሆኑ አበረታች መሆኑን ጠቅሰዋል።

በመጨረሻ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን፥ ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄነራል አደም መሃመድ፥ የሰላም ሚኒስትሯ ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል እና ከፍተኛ የጦር መኮንኖችን ጨምሮ የሃገር መከላከያ ዋና ፅ/ቤት ህንፃ ግንባታ ሂደት በመጎብኘት በምድር ጦር ቅጥር ግቢ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ላይ ተሳትፈዋል።

በሃይለኢየሱስ ስዩም

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.