Fana: At a Speed of Life!

የኮቪድ19 ስርጭት መስፋፋት ከቀጠለ የምርት አቅርቦት ላይ ክፍተት እንዳይፈጠር አማራጭ ስትራቴጂ ተዘጋጅቷል – አቶ መላኩ አለበል

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 27፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኢትዮጵያ የኮቪድ19 ስርጭት መስፋፋት ከቀጠለ የምርት አቅርቦት ላይ ክፍተት እንዳይፈጠር መንግስት አማራጭ ስትራቴጂ ማዘጋጀቱን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል ገለጹ።

የኮቪድ19 በመላው ዓለም በሰው ልጆች ጤና ላይ ካደረሰው ጉዳት ትይዩ በኢኮኖሚው ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱ ይነገራል።

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በነበራቸው ቆይታ፥ ከአርሶ አደሩ ማሳ ወደ ህብረተሰቡ ምርትን የሚያሰራጩ የህብረት ስራ ማህበራትን ለማጠናከር 800 ሚሊየን ብር በላይ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የኮቪድ19 የስርጭት የቢሆን ትንበያዎች ወደ አራተኛው ምዕራፍ በፍጥነት እየተንደረደረ መሆኑ ተጠቁሞ፥ የንግድ እና የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በሀገሪቱ በመጋቢት ወር ቫይረሱ ከገባበት ጊዜ አንስቶ ዓለም አቀፍ ሁኔታዎችና የሀገር ውስጥ የኢኮኖሚ ሁናቴን ያገናዘበ ስትራቴጂ አዘጋጅቷል።

ይህ የቫይረሱ መስፋፋት በጨመረ ቁጥር ሊያደርስ የሚችለውን ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ለመቋቋም የተዘጋጀው ስትራቴጂ በተለይ የፍጆታ እቃዎች ወደ ህብረተሰቡ በቅርብ የሚደርስበትን ስልት የዘረጋ ነው ተብሏል።

በዚህም የሀገር ውስጥ ምርትን ወደ ገበያው በበቂ ደረጃ የማሰራጨት ሀላፊነት ያለባቸው የህብረት ስራ ማህበራትን ጠንካራ ማድረግ ይጠበቃልም ነው ያሉት።

በዚህም በስትራቴጂው አማራጭነት ምርትን የህብረት ስራ ማህበራት በተሽከርካሪ ጭምር የሚያሰራጩበት መንገድ ታስቧል።

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል እንደሚሉትም በስትራቴጂው ከውጭ የሚገቡ ምርቶች በወደብ አካባቢ የመዘግየት ምክንያት እንዳይደረድሩም የትራንስፖርት እና የሎጂስቲክስ ግብረ ሀይል ከወዲሁ ተቋቁሞ ወደ ስራ ገብቷል።

ምናልባት እንቅስቃሴዎች የሚገቱበት ሂደት እንኳን ቢመጣ በመላው ሀገሪቱ ከ1 ሺህ 600 በላይ የመንደር የግብይት ማዕከላት መዘጋጀቱን አውስተዋል።

የንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽን የአትክልትና ሰብሎችን ለህብረተሰቡ የሚያቀርብበትን አሰራር እንዲተገብር እየተሰራ መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሩ ተጨማሪ የማቅረቢያ መንገዶችንም እንዲያመቻች መታቀዱንም አንስተዋል።

አያይዘውም ህብረተሰቡ በግብይት ቦታዎች የሚያደርጋቸውን ንክኪዎች እንዲያቆም እና ርቀቱን እንዲጠብቅ በተለይ በገንዘብ ልውውጥ ወቅት ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲደረግ አሳስበዋል።

በሀይለየሱስ መኮንን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.