Fana: At a Speed of Life!

ደቡብ ሱዳን በየትኛውም መንገድ ኢትዮጵያን የሚጎዳ ተግባር አትፈፅምም- አምባሳደር ጀምስ ፒፒያ ሞርጋን

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 27፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ደቡብ ሱዳን በየትኛውም መንገድ ኢትዮጵያን የሚጎዳ ተግባር መፈፀም እንደማትችል በኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳን አምባሳደር ጀምስ ፒፒያ ሞርጋን ገለፁ።

አምባሳደር ጀምስ ፒፒያ ሞርጋን ደቡብ ሱዳን ከሰሞኑ ለግብጽ የጦር ሰፈር እንድትገነባ ፈቃድ ሰጥታለች በሚል የሚናፈሰው መረጃ  ዙሪያ በዛሬው እለት መግለጫ ሰጥተዋል።

አምባሳደሩ በመግለጫቸውም ከሰሞኑ ደቡብ ሱዳን ለግብፅ በፓካግ የጦር ሰፈር እንድትገነባ መሬት ሰጥታለች የተባለው ፍፁም ሀሰት እንደሆነ ገልፀዋል።

መረጃውን የሚያሰራጩ ቡድኖች የሁለቱን ሀገራት ትብብር የማጠልሸት ፍላጎት ያላቸው ናቸው ሲሉም ተናግረዋል።

ደቡብ ሱዳን ችግር ለይ በወደቀችበት ጊዜ ሁሉ ኢትዮጵያ ከጎና አለች ያሉት አምባሳደሩ፥ ይህንን ውለታ ደቡብ ሱዳናውያን መቼም አይዘነጉትም ብለዋል።

ኢትዮጵያ ችግሮችን በውይይት እንደምትፈታ እምነት አንዳላቸውም አምባሳደር ጀምስ ፒፒያ ሞርጋን ገልፀዋል።

በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ግን ደቡብ ሱዳን ከኢትዮጵያ ጎን እንደምትሰለፍ አረጋግጠዋል።

ኢትዮጵያን ለማጥቃት ያሰበ ሀይል በደቡብ ሱዳን በኩል ሊመጣ ቢያስብ እንኳ ቀድሞ የሚጋፈጠው ደቡብ ሱዳናውያንን ነው ሲሉም ተናግረዋል።

ደቡብ ሱዳን ኢትዮጵያ በራሷ ግዛት የራሷን ተፈጥሯዊ ሀብት የመጠቀም መብቷን ሙሉ በሙሉ እንደምታከብምርም አምባሳደሩ ገልፀዋል።

የደቡብ ሱዳን የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር መስሪያ ቤት በትናንት ባወጣው መግለጫ ጁባ ግብፅ በፓጋክ አካባቢ የጦር ሰፈር ትገነባ ዘንድ ይሁንታ ሰጥታለች በሚል እየተናፈሰ ያለው ወሬ ከእውነት የራቀ እና መሰረተ ቢስ መሆኑን መግለፁ ይታወሳል።

በአላዛር ታደለ

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.