Fana: At a Speed of Life!

ጁንታው ለህጻናት የገቡ አልሚ ምግቦችን እየዘረፈ ለታጣቂዎቹ እያደለ ነው

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 19፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) የሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር አሸባሪው ህወሓት ለህጻናት የገቡ አልሚ ምግቦችን እየዘረፈ ለታጣቂዎች ማደሉን አወገዘ፡፡

ቡድኑ በጦርነት ወቅቶች ህጻናት ከሚደርሱባቸው አካላዊና አዕምሯዊ ጉዳቶች በቶሎ አገግመው ብቁ ዜጋ እንዲሆኑ ለማስቻል ተዘጋጅተው በእርዳታ የሚቀርቡ አልሚ ምግቦችን በመዝረፍ ለታጣቂዎቹ ማድረጉ ተነስቷል፡፡

ይህን ተግባሩን ዓለም አቀፉ ህብረተሰብ እንዲያወግዝ ጥሪ ቀርቧል፡፡

የሚኒስቴሩ የህግ ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ደረጄ ተግይበሉ እንደገለጹት÷ በቅርቡ በምርኮኞች እጅ የተገኙ የህጻናት አልሚ ምግቦች በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸውን ህጻናት ለመደገፍ ታስበው የቀረቡ ናቸው፡፡

አሸባሪው ህወሓት እነዚህን አልሚ ምግቦች እየዘረፈ ለታጣቂዎቹ እያደለ እንደሚገኝ ሰሞኑን ከጦር ሜዳ ግንባር የተገኙ መረጃዎች ይፋ ማድረጋቸውን አቶ ደረጄ ጠቁመዋል፡፡

ይህ የቡድኑ ተግባር አስነዋሪ እና ሊወገዝ የሚገባ እንደሆነ አመልክተው÷ አሸባሪው ለትውልድ ደንታ ቢስ እና ትውልድ ገዳይ መሆኑን በተጨባጭ ያሳየ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ህጻናቱን ከእናታቸው ጉያ እየነጠቁ ለጦርነት ተግባር ማሰለፋቸው ሳያንስ ለተቀሩት ጨቅላ ህጻናት የገቡ አልሚ ምግቦችን ላልተገባ ተግባር መጠቀሙ ህጻናቱ ተደራራቢ ችግር ላይ እንዲወድቁ አድርጓልም ነው ያሉት፡፡

ይህ ተግባሩ በዓለም አቀፍም ሆነ በሃገር ውስጥ ህግ ወንጀል እንደሆነ ሊታወቅ እንደሚገባ ገልጸው÷ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም ጉዳዩ በጣም እንደሚያሳስበው አመላክተዋል፡፡

ህጻናት ምግብ እንዳያገኙ ለእነሱ የመጣን አልሚ ምግብ ለራስ ፍጆታ መጠቀም ከቅጣቶች ሁሉ የባሰ ቅጣት ከጦርነትም በላይ በርሃብ እንዲያልቁ ማድረግ የጭካኔ መጨረሻ ጥጉ ነው ብለዋል ዳይሬክተሩ፡፡

ህጻናቱ ከዚህ ችግር እንኳን ቢተርፉ በቂ ምግብ ያላገኙ ስለሚሆኑ የመቀንጨር እና ለተለያዩ በሽታዎች የመጋለጥ ችግር ያጋጥማቸዋል ማለታቸውን ኢፕድ ዘግቧል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.